ፈልግ

ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ውሳኔ አስተላልፏል ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ውሳኔ አስተላልፏል  (ANSA)

የተ.መ. ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስራኤል ጅምላ ጭፍጨፋን እንድታቆም ማዘዙ ተነገረ

የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዳኛ ዶኖጉዌ እንዳሉት “ፍርድ ቤቱ በክልሉ በሚገኙ ህዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ድርጊት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እና አሁንም ድረስ ያልቆመው የህይወት መጥፋት እና የሰዎች ስቃይ በጣም ያሳስበዋል” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ ባቀረበችው የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ምክንያት በእስራኤል ላይ አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጫና መፍጠሩ ተገልጿል።

በሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ ያቀረበችው ክስ የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው በማለት ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ወስኖ ቆይቷል። ሆኖም ጉዳዩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስራኤል ክሱን መሠረተ ቢስ በማለት ስታጣጥል መቆየቷ ይታወቃል። 

በደቡብ አፍሪካ የቀረበው ማስረጃ ያልቀረበበት የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ያልተጠበቀ ቢሆንም፥ ፍርድ ቤቱ ባለፈው አርብ ባወጣው ጊዜያዊ ውሳኔ እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከሞት ወይም ከጉዳት እንድትከላከል እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን እና ሰብአዊ ዕርዳታዎችን መስጠት የምትችልባቸውን እርምጃዎች እንድትወስድ ትእዛዝ ሰጥቷል።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ዳኛ ዶኖጉዌ እንዳሉት “ፍርድ ቤቱ በክልሉ እየደረሰ ያለውን የሰው ልጅ ሰቆቃ ምን ያህል እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል፥ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የህይወት መጥፋት እና የሰዎች ስቃይ በጣም ያሳስበዋል” ብለዋል።

ምንም እንኳ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ሁለት ጊዜ በአብላጫ ድምፅ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ቢወስንም ይህን ተግባራዊ ማድረግ ተስኖታል።

የፍርድ ቤት ውሳኔዎች አስገዳጅ እንደሆኑ ቢታወቅም፥ ነገር ግን የማስፈጸሚያ ዘዴዎች እንደሌላቸው ብዙ ጊዜ ይነገራል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ደቡብ አፍሪካ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቀች ሲሆን፥ የደቡብ አፍሪካ ጠበቆች እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ያለችው ለወራት የዘለቀ የቦምብ ጥቃት እ.አ.አ. በ1948 የወጣውን የዘር ማጥፋት ስምምነትን የጣሰ እና ጋዛን የማጥፋት ዓላማው ‘በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ደረጃ ድጋፍ የተሰጠው ነው’ ሲሉ ይከራከራሉ።

እስራኤል ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀል የሚገልጸውን እና ሃገራት ወንጀሉን እንዳይፈፅሙ የሚያስገድደውን ስምምነት ከፈረሙ ሃገራት ውስጥ አንዷ እንደሆነችም ይታወቃል።

ጊዜያዊ ብይኑ ከተገለጸ በኋላ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የዘር ማጥፋት ውንጀላውን በማጣጣል ‘ይህ ክስ ውሸት ብቻ ሳይሆን አጸያፊ ነው፥ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ጨዋ ህዝቦች ውሳኔውን ውድቅ ሊያደርጉት ይገባል’ ካሉ በኋላ ‘እስራኤል ዓለም አቀፍ ህግን በማክበር እራሷን እና ዜጎቿን መከላከሏን ትቀጥላለች’ ብለዋል። በማከልም “ይህ ጦርነት ፍፁም ድልን እስከምናገኝ ድረስ ይቀጥላል” በማለት ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውሳኔውን በደስታ በመቀበል ሁሉም ግዛቶች በፍርድ ቤቱ የታዘዙ ጊዜያዊ እርምጃዎች መተግበራቸውን እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።

በተያያዘ ዜና የእስራኤሉ ኤል-አል አየር መንገድ ከመጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ ጆሃንስበርግ የሚያደርገውን በረራ እንደሚያቆም ያስታወቀ ሲሆን፥ ኩባንያው ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ የቻለው ከፍተኛ የበረራ እንቅስቃሴ በመቀነሱ ምክንያት እንደሆነም ጠቅሷል።
 

29 January 2024, 16:17