ፈልግ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ - የፋይል ፎቶ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ - የፋይል ፎቶ   (ANSA)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የፍልስጤምን እንደ ሃገር የመመስረት ጥያቄን ተቃወሙ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤምን መንግስት የመመስረት ሃሳብ በድጋሚ ውድቅ እንዳደረጉ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ እስራኤል ጦርነቱን አቁማ ሙሉ በመሉ እንድትወጣ እና ሃማስ በጋዛ ስልጣኑን እንዲይዝ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ውድቅ ማድረጋቸውን በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል።

ኔታንያሁ እስራኤል በሁሉም የፍልስጤም ግዛቶች ላይ የጸጥታ ቁጥጥር ማድረግ አለባት ሲሉ ካረጋገጡ በኋላ፥ ሲደረጉ የነበሩ ሁኔታዎች ወደፊት የፍልስጤም መንግስት ከመመስረት ጋር የሚቃረን ነው ብለዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየቶች ወደፊት ፍልስጤም እንደ ሀገር እንድትመሰረት ቃል እንዲገቡ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት በአስተዳደራቸው ላይ የሚያደርሱትን ጫና ለመቋቋም ሆን ተብለው የተነገሩ ናቸውም ተብሏል።

ኔታንያሁ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አርብ ዕለት በስልክ ባደረጉት ውይይት ስለ ፍልስጤም ግዛቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ እንደተወያዩ መረጃዎች አመላክተዋል።

ችግሩን ለመፍታት የሁለትዮሽ ስምምነት ይፈልጋል

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፍልስጤማውያን የራሳቸውን ሀገር የመመስረት መብታቸው በሁሉም ዘንድ እውቅና ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ ዜና፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ብፁዓን ጳጳሳት ሁለቱ ሀገራት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ወደ መፍትሔ ሃስብ እንዲመጡ ያለማቋረጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኔታንያሁ ከተለያዩ ሃገራት ድጋፍ ማጣት የጀመረው በሃገር ውስጥ ተቃውሞው እየበረታባቸው በመምጣቱ እና በሃማስ ታግተው አሁንም ድረስ በጋዛ ውስጥ ያሉ ታጋቾች እጣ ፈንታ ላይ ምንም መፍትሄ ስላላመጡ እንደሆነ አንዳንድ ዘገባዎች ያሳያሉ።

የታጋቾቹ ዘመዶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ቅዳሜ እለት በቴል አቪቭ ተሰብስበው ታጋቾቹ ወደቤታቸው በሠላም ይመለሱ ዘንድ ኔታንያሁ የሠላም ስምምነት እንዲያረጉ ጠይቀዋል።

ባለፈው ህዳር በኳታር አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሀማስ አግቷቸው ከነበሩት 240 ሰዎች ውስጥ 100 የሚሆኑትን ሲለቅ በምትኩ እስራኤል ያሰረቻቸውን 240 ፍልስጤማውያንን መልቀቋ ይታወሳል።

ጦርነት የሰብአዊ እርዳታን ያደናቅፋል

በሌላ ዜና የቦምብ ድብደባው እና ውጊያው ተጠናክሮ በመቀጠሉ በቅርቡ ከኳታር የተላከውን ጨምሮ በጋዛ የአስቸኳይ የህክምና እና የሰብአዊ አቅርቦቶችን ስርጭት ማደናቀፉ የተነገረ ሲሆን፥ እርዳታው በኳታር እና በፈረንሳይ ሸምጋይነት የተደረሰው ስምምነት አካል የሆነ የመጀመሪያው ጭነት እንደሆነም ተገልጿል። በዚህም በደርዘን የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን ታጋቾች መድሃኒቱን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በካን ዮኒስ ተደብቀዋል ብላ የምታስባቸውን የሃማስ ባለስልጣናትን ፍለጋ ጦሯ ወደ ደቡብ ጋዛ መግፋቱን ቀጥለዋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ቅዳሜ በደቡባዊ ሊባኖስ በጭነት መኪና ላይ ባነጣጠረ የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውም ተነግሯል።
 

23 January 2024, 14:17