ፈልግ

በዌስት ባንክ የሚገኝ በኤጀንሲው የሚተዳደር የዩኒቨርሲቲ በዌስት ባንክ የሚገኝ በኤጀንሲው የሚተዳደር የዩኒቨርሲቲ   (AFP or licensors)

ሃገራት በጋዛ ውስጥ እየሰራ ለሚገኘው የተ.መ. ኤጀንሲ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ ማቆማቸው ተነገረ

የሐማስ ታጣቂዎች መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የእስራኤልን ድንበር ጥሰው በመግባት በፈጸሙት መብረቃዊ ጥቃት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲ ሠራተኞች ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት እሰራኤል ካወጣች በኋላ አሜሪካን ጨምሮ እንግሊዝ እና ጀርመን በጋዛ ለሚገኙ የፍልስጤም ስደተኞች እርዳታ በማስተባበርና በማሰራጭት ከፍተኛ ሥራ ለሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ የሚያደርጉትን ድጋፍ በማቋረጣቸው የተባበሩት መንግስታት ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ እርዳታ በማስተባበርና በማሰራጭት ከፍተኛ ሥራ የሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ (በእንግሊዝኛ ምሕጻረ ቃል UNRWA) ለጋዛ ድጋፍ ማድረግ ያቆሙ አገራትን አውግዟል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ውሳኔውን “አስደነጋጭ” ያሉት ሲሆን፥ ይህ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ከ2 ሚሊዮን ለሚልቁ የጋዛ ነዋሪዎች ምግብና መጠለያን በዋናነት ሲያቀርብ እንደቆየም ተናግረዋል።

አሁን ላይ በዋናነት የገንዘብ ድጋፍ ለኤጀንሲው ይሰጡ የነበሩት ዩኬና ሌሎች የምዕራብ አገራት ልገሳውን ያቆሙ ሲሆን፥ ይህም የሆነው ሐማስ በፈጸመው መብረቃዊ ጥቃት የዚህ ኤጀንሲ ሠራተኞች ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት እሰራኤል በማውጣቷ ነው።

የኤጀንሲው ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ “ሁለት ሚሊዮን ሰው ሕይወቱ የተመሠረተው በዚህ እርዳታ ነው” ሲሉ ዕርዳታው ከቆመ የሚከሰተውን የአደጋውን ስፋት ለማሳየት ሞክረዋል።

እርዳታ መስጠት ያቆሙት ዩኬን ጨምሮ ስምንት አገራት ሲሆኑ እነሱም አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ እና አሜሪካ ናቸው።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂዎች በደቡብ እስራኤል ላይ ባደረሱት ጥቃት 12 የኤጀንሲው ሰራተኞች እጃቸው አለበት የሚል ዘገባ እስራኤል ካወጣች በኋላ በጋዛ እርዳታ በማስተባበርና በማሰራጭት ከፍተኛ ሥራ ለሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ ቢያንስ 9 ሀገራት ሲያደርጉት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ማቆማቸውን ሰሞኑን አሳውቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጀርመን እና ብሪታንያ የተባበሩት መንግስታት ከሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞቹ ውስጥ አንዱ እና ትልቁ ለሆነው ለዚህ የእርዳታ ኤጀንሲ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ ካቆሙት ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

ይህ ተቋም እ.አ.አ. በታህሳስ 8 ቀን 1949 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ንዑስ አካል ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን፥ በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ1950 ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።

ሌሎች ሃገራትም ለጊዜው የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚያቆሙ የተነገረ ሲሆን፥ እነዚህም ሃገራት አውስትራሊያ፣ ጣሊያን፣ ካናዳ፣ ፊንላንድ፣ ጃፓን እና ኔዘርላንድስ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ በዌስት ባንክ (ምስራቅ እየሩሳሌም ጨምሮ) በጋዛ ሰርጥ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ እና ሶሪያ ውስጥ የፍልስጤም ስደተኞችን በትምህርት፣ በጤና እንክብካቤ፣ በእርዳታ እና በማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ጥበቃ፣ የካምፕ መሠረተ ልማት እና ማሻሻያ፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ በመስጠት ትልቅ ሥራን እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ሰኞ ዕለት ኤጀንሲው እንዳስታወቀው የገንዘብ ድጋፉ ካልቀጠለ ከጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋዛ እና በክልሉ ውስጥ ሲተገብር የነበሩትን ስራዎችን መቀጠል እንደማይችል ተናግሯል።

ሰራተኞቹ በመስከረም 26ቱ ጥቃት መሰተፋቸው ስለተነገረ የስራ ውላቸው ተቋርጧል

የኤጀንሲው ቃል አቀባይ “የገንዘብ ድጋፉ እንደገና ካልቀጠለ ኤጀንሲው ጋዛን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከጥር ወር መጨረሻ በኋላ አገልግሎቱን እና ሥራውን መቀጠል አይችልም” ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ድጋፋቸውን ያቆሙትን ለጋሽ ሀገራት የተማፀኑ ሲሆን፥ ኤጀንሲው እና ፍልስጤማውያን በደርዘን የሚቆጠሩ ሰራተኞች ፈፅመዋል በተባለው ድርጊት ሊቀጡ እንደማይገባ አሳስበዋል።

መስከረም 26 በደረሰው የሐማስ ጥቃት ተሳትፈዋል የተባሉት ዘጠኝ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ ሰራተኞች ሥራ ማቆማቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊ ተናግረዋል።

ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ማንኛውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ በሽብር ተግባር ላይ ከተሳተፈ በህግ እንደሚጠየቅ እና በወንጀልም እንደሚከሰስ አሳስበዋል። አክለውም የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የምርመራ መዋቅር የሆነው የተባበሩት መንግስታት የውስጥ ቁጥጥር አገልግሎት ቢሮ ምርመራ እንዲያደርግ መጠየቁንም አስምረውበታል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ግጭቱ ሲያበቃ ይህ ተቋም በጋዛ ምንም አይነት ሚና እንደማይኖረው ገልፀዋል።
 

30 January 2024, 14:58