ፈልግ

የአሜሪካውፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ንግግር ሲያደርጉ - 20/05/2016 ዓ.ም. የአሜሪካውፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ንግግር ሲያደርጉ - 20/05/2016 ዓ.ም.  (AFP or licensors)

ኢራን በዮርዳኖስ በሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመው ጥቃት እጇ እንደሌለበት አስተባበለች

ኢራን በዮርዳኖስ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሰፈር ላይ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን በገደለው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት እጇ እንደሌለበት አስተባብላለች።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እሁድ እለት ስትራቴጂካዊ በሆነው በሶሪያ እና ዮርዳኖስ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውንና 'ታወር 22' ተብሎ የሚታወቀውን የአሜሪካ ጦር ሰፈር በሰው አልባ አውሮፕላን በደረሰ ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውንና በደርዘን የሚቆጠሩት ደግሞ መቁሰላቸውን ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ ይገኛል።

ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ ዋሽንግተን በአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሎ በሚታሰበው ጥቃት ጀርባ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን፥ ፕሬዝደንት ባይደን አሜሪካ ለጥቃቱ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኢራን በዚህ ጥቃት እጄ የለበትም ስትል የሚቀርብባትን ክስ አስተባብላለች።

የወታደሮቹን ግድያ ተከትሎ የአሜሪካ ሪፐብሊካኖች ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ወታደሮቹን ለጥቃት አጋልጠዋቸዋል የሚል ክስ አቅርበው፥ ባይደን በኢራን ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እንዲሰነዝሩም ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።

የኢራን ማስተባበያ

ሆኖም ኢራን ከድርጊቱ ጀርባ እጇ እንደሌለበት ያስተባበለች ሲሆን፥ ክሱንም መሠረተ ቢስ ነው ካለች በኋላ፥ በምንም ዓይነት መልኩ የተቃዋሚ ቡድኖች ውሳኔ ላይ እንዳልተሳተፈች ተናግራለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢራን ተወካይ እንደገለጹት፥ ቴህራን ከጥቃቶቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላት በመግለጽ፥ “ክስተቱ በአካባቢው በዩናይትድ ስቴትስ ጦር እና በተቃዋሚ ቡድኖች መካከል ያለው ግጭት አካል እንደሆነ እና ጥቃቶቹ ተለዋዋጭ የሆኑ የበቀል እርምጃዎች ናቸው” ብለዋል።

በአማን የሚገኘው የዮርዳኖስ መንግስት ጥቃቱን በማውገዝ ድንበሩን ለማስጠበቅ እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከዋሽንግተን ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ኢራን በገንዘብ የምትደግፋቸው የሁቲ አማፂያን ካለፈው ኀዳር ወር ጀምሮ ቀይ ባሕርን አቋርጠው በሚጓዙ የንግድ መርከቦች ላይ ከ30 በላይ ጥቃቶች እንደሰነዘሩ የሚታወስ ሲሆን፥ የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት አማፂያኑን ሳንደመስስ አርፈን አንቀመጠም ብለው እንደ ነበር ይታወሳል።

ባለሥልጣናቱ ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህ ቡድን የሚያደርሰውን አደጋ ለመግታትም ሆነ ለማምከን ተጨማሪ እርምጃዎችን ከመወሰድ አንታቀብም፤ የቀይ ባሕር ቀጣና እስኪረጋጋ ድረስ እንቀጥላለን” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በኢራቅ እና ሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ብዙ ጊዜ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ይነገራል።

እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ያለውን እንቅስቃሴ ቀጥላለች

በሌላ ዜና የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በጋዛ ሰርጥ ባደረሰው ከፍተኛ ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ የሃማስ ታጣቂዎችን መግደሉን ገልጿል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የእርቅ ስምምነቶችን በማረጋገጥ በሃማስ የተያዙ የእስራኤል ታጋቾች በዚህ ሳምንት ሊለቀቁ እንደሚችሉ ይጠበቃል ተብሏል።
 

30 January 2024, 12:01