ፈልግ

የእስራኤል ወታደሮች በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር አከባቢ የእስራኤል ወታደሮች በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር አከባቢ 

የጦርነቱ መስፋፋት የሊባኖስን ሰብዓዊ ቀውስ እያባባሰው እንደሚገኝ ተገለጸ

በእስራኤል ጦር እና ሊባኖስ ውስጥ በሚገኙት የሄዝቦላህ ታጣቂዎች መካከል ከእስራኤል ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ እየተደረገ ያለው ግጭት እየተባባሰ በሄደ ቁጥር በሺዎች የሚቆጠሩ የሊባኖስ ቤተሰቦች ከደቡብ የሊባኖስ ክፍል ለቀው እየወጡ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእስራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ታጣቂዎች መካከል የቀጠለው የድንበር ላይ ግጭት መባባስ ቀድሞውንም ችግር ውስጥ ለነበረችው ሊባኖስ ሌላ ትልቅ ሰብአዊ ቀውስ ያስከትላል ተብሏል።

በሃማስ እና በእስራኤል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት መስከረም 26 ጀምሮ ደቡብ ሊባኖስ በየቀኑ ማለት ይቻላል በኢራን በሚደገፉ ሚሊሻዎች እና በእስራኤል ወታደሮች መካከል ወረራ፣ ድብደባ እና የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበረና በሺዎች የሚቆጠሩ የሊባኖስ ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው እንዲሰደዱ እንዳስገደዳቸው ተዘግቧል።

ክርስቲያን ቤተሰቦችን ጨምሮ 82,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በግጭቱ ከ82,000 በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ እና ከእነዚህም ውስጥ 20 በመቶው ህጻናት እንደሆኑ ተገልጿል።

ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 4 ባለው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ በመጨመር ከ26,323 ወደ 46,325 ሰዎች መፈናቀላቸው እና ባለፉት ሳምንታት ከ18,000 በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው በመውጣታቸው ሌላ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

አብዛኞቹ ከእስራኤል ጋር በድንበር የሚዋሰኑት የአከከባቢው መንደር ነዋሪዎች ሸሽተው መውጣታቸው ነው የተነገረው። በቅርቡ ኤ.ሲ.ኤን. የተባለው የቤተክርስቲያን በጎ አድራጊ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንዳሳወቀው የክርስቲያን መንደሮችም በተኩስ ልውውጡ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

ከአምስት የተፈናቀሉ ሊባኖሳዊያን መካከል አንዱ በአሁኑ ጊዜ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ባሉ ቤተሰቦች የሚስተናገዱ ሲሆን፥ 16 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በኪራይ ቤቶች እንደሚኖሩ ተነግሯል። ነገር ግን እንደ ‘ላ ኦሪየንት ሌ ጆር’ የሚባለው የሊባኖስ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ በሊባኖስ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር ምክንያት ይህ አማራጭ ለአብዛኛዎቹ የማይመች አድርጎታል ብሏል።

በደቡብ ሊባኖስ የሚገኘው የግብርና ዘርፍ በግጭቱ ተጎድቷል

ውጊያው 80 በመቶውን የደቡብ ሊባኖስ የሀገር ውስጥ ምርትን የሚወክለውን የግብርናውን ዘርፍ በእጅጉ ጎድቷል። ግጭቱ የጀመረው የመኸር መሰብሰቢያ ወቅት በመሆኑ፥ የእስራኤል ጦር እየወሰደ ባለው ጥቃት ምክንያት ብዙ የወይራ ዘይት ግብአቶች እና የፍራፍሬ ሰብሎች በመውደማቸው እጅግ በርካታ ቤተሰቦች ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው አጥተዋል ተብሏል።

በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ወደ ሙሉ ክልላዊ ጦርነት እየተሸጋገረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ውጥረትን እየጨመረ ከመምጣቱ በተጨማሪ፥ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለው የግጭቶች መባባስ የሴዳርስን ምድር ቀድሞውንም በፖለቲካ ቀውስ እና በሙስና የተጨማለቀ የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በቋፍ የነበረውን የሰብአዊ ሁኔታ በእጅጉ እያባባሰ መሄዱ አሳሳቢ ነው ተብሏል። ሊባኖስ በነፍስ ወከፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ካሉባቸው አገሮች አንዷ ስትሆን አብዛኞቹ ከሶሪያ የመጡ እንደሆነም ተመላክቷል።

የነዚህ ውስብስብ የሆኑ የበርካታ ቀውሶች ስብስብ ሰፊ ድህነትን፣ የህዝብ አገልግሎቶች ውድቀትን እና የማህበረሰብ ውጥረቶችን እያባባሰ እንዲሁም በሶሪያውያን ስደተኞች ላይ ጥላቻን እያሳደገ መምጣቱም ተነግሯል።

በሊባኖስ ውስጥ ያለው ድህነት መጨመር

በአስከፊው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የዋጋ ንረት እየጨመረ በመምጣቱ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የሊባኖስ እና የሶሪያ ስደተኞች የምግብ ዋስትና እጦት ላይ እንደሆኑ እና ይህ ቁጥር አሁን የበለጠ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል ተብሏል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል የጤና እንክብካቤን ጨምሮ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለመሸፈን ይቸገራሉ። በገንዘብ ችግር እና በመድሃኒት እጦት ምክንያት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በእጅጉ ቀንሷል። በቂ ደመወዝ ባለመኖሩ ብዙ የጤና ባለሙያዎች ሀገሪቱን ለቀው ወጥተዋል፥ የነዚህም ድምር ውጤቶች ወሳኝ የሆነውን ሁለተኛ ደረጃ የጤና አገልግሎት ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል።

እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ 1.2 ሚሊዮን ሊባኖሳውያን ህጻናት መካከል ከአስር በመቶ በላይ የሚሆኑት በዋነኛነት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ከትምህርት ውጪ ናቸው። በተጨማሪም ከ715,000 የሶሪያ ስደተኞች መሃል 60 በመቶው ከመደበኛ ትምህርት ውጪ ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ውስጥ 47,000 የሚሆኑት ብቻ መደበኛ ያልሆነ ትምህርት እንደሚያገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
 

17 January 2024, 14:21