ፈልግ

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

አሜሪካ፥ እስራኤል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የምታደርሰውን ጉዳት እንድትቀንስ ጠየቀች

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ሎይድ ኦስቲን፥ እስራኤል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የምታደርሰውን ጉዳት እንድትቀንስ መጠየቋን ገልጸው፥ መንግሥታቸው በጋዛ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን ስለማድረግ መወያየቱን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዋና ጸሐፊው አቶ ሎይድ ኦስቲን በቴል አቪቭ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ዋሽንግተን ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥል፥ ነገር ግን በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመቀነስ ወደ ዝቅተኛ ወታደራዊ ተግባራት መሸጋገር እንዳለባት ተወያይቷል። የዋና ጸሐፊው የአቶ ሎይድ ኦስቲን አስተያየት ይፋ የሆነው የእስራኤል አየር ኃይል በጃባሊያ 110 ሰዎችን መግደሉን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ካስታወቁ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እንደ ሆነ ታውቋል።

ይሁን እንጂ ጥቃቱን በማስመልከት ከእስራኤል በኩል የወጣ ዝርዝር አስተያየት ባይገኝም፥ እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምትፈጽመው ጥቃት በአሸባሪዎች መሠረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል።

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፥ ጦርነቱ በአስቸኳይ በዘላቂነት እንዲቆም በሚለው ሃሳብ ላይ በተደጋጋሚ ከተከራከረበት በኋላ ድምጽ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል።

በጋዛ ያለው ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይን እና ጣሊያንን እየጎበኑ ለሚገኙት የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ዴቪድ ካሜሮን ቀዳሚ አጀንዳቸው እንደሆነ ታውቋል። ከጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ለመገናኘት ወደ ሮም ከማቅናታቸው አስቀድመው በፓሪስ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ጋር ይገናኛሉ።

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ መስከረም 20/2016 ዓ. ም. የእስራኤልን ድንበር ጥሶ 1,200 ሰዎችን መግደሉ እና 240 ሴቶችን እና ሕጻናትን ማገቱ ይታውሳል። በጋዛ የሚገኘው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ 19,400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና 52,000 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።

 

20 December 2023, 18:06