ፈልግ

የእስራኤል ወታደሮች በካን ዩኒስ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄዱ የእስራኤል ወታደሮች በካን ዩኒስ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄዱ  

እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ያለውን የቦምብ ጥቃት አጠናክራ እንደምትቀጥል ተነገረ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለጋዛ ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲደረግ ጥሪ እያስተላለፈ ባለበት ወቅት፥ የእስራኤል ጦር ምንም እንኳን ውጊያው ከባድ እንደሚሆን ቢያምንም በጋዛ የሚያደርገውን ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት እስራኤል በደቡባዊ እና ሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ የምታካሄደውን የምድር ጦር ዘመቻዋን እያስፋፋች ነው ብለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒንያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው አገራቸው ከሐማስ ጋር የገባችው ጦርነት ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት ነው ማለታቸውም ተነግሯል።

ከጥቂት ቀናት በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለጋዛ ሰርጥ ተጨማሪ እርዳታን የሚደግፍ የውሳኔ ሃሳብ ማጽደቁ እና በእስራኤል እና በሃማስ መካከል አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን የእስራኤል አጋሮች አገሪቱ ለሰላማዊ ሰዎች የምታደርገውን ጥበቃ እንድታጠናክር እያሳሰቡ ይገኛሉ።

በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኩል ለጠረጴዛ የቀረበው እና ከቀናት ውይይቶች በኋላ የተደረገው የድጋፍ ድምጽ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል እና የእስራኤል ወሳኝ አጋር የሆነችውን የዩናይትድ ስቴትስን የማገጃ ድምጽ ለማስቀረት እንደሆነ ተነግሯል። ሆኖም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የእርዳታ አቅርቦት ላይ ችግር እየፈጠረ ያለው የእስራኤል የማያቋርጥ ጥቃት ነው ብለዋል።

መላው ህዝብ በከፍተኛ እጥረት እየተሰቃየ ነው

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ የተደረገው ግምገማ እንደሚያሳየው የጋዛ ህዝብ በሙሉ በከፍተኛ እጥረት እየተሰቃየ እንደሆነ ነው። የእርዳታ ኤጀንሲዎች እንደሚገልጹት ወደ ክልሉ የሚደርሰው ውስን አቅርቦቶች ለፍጆታ ከሚያስፈልገው ጋር ሲነፃፀር ምንም አይገናኝም ብለዋል። በተጨማሪም በወታደራዊ ዘመቻው እና በነዳጅ እጥረት ምክንያት ስርጭቱ ተስተጓጉሏል ተብሏል።

ጦርነቱ ተባብሶ ቀጥሏል

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቀጠል ቆርጫለሁ ማለቷ፥ ሃማስ ታጋቾችን መልቀቅ የሚቻለው እስራኤል ጦርነቱን ለማቆም ከተስማማች ብቻ ነው ሲል የሰጠውን መግለጫ በትክክል ውድቅ ያደርገዋል ተብሏል።

እየተደረገ ያለው የተኩስ አቁም ድርድር ቢቀጥልም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግጭት ባለፉት 24 ሰዓታት ተባብሶ መቀጠሉም ተነግሯል። በእነዚህም ጊዜያት ውስጥ የእስራኤል ጦር በአየር፣ በባህር እና በየብስ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ጥቃቱን ሲፈፅም እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ የተካሄደው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ በኋላ ከ2,000 በላይ የፍልስጤም ተዋጊዎች በጋዛ መገደላቸውን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚንስቴር የእስራኤል ጦር ትናንት እሁድ በመጠላያ ጣቢያ ላይ ባደረሰው የቦምብ ድብደባ ቢያንስ 70 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

ሚኒስቴሩ ከመስከረም 26ቱ ጥቃት ወዲህ በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ መሆኑን ይገልጻል። ከእነዚህ ሟቾች መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው። ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከ54 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ገልጿል።
 

25 December 2023, 15:13