ፈልግ

እስራኤላውያን በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በሚገኙ ቤቶች ላይ ጥቃት ካደረሱ ከአንድ ቀን በኋላ ፍልስጤማውያን ከአደጋው የተረፉትን ሲፈልጉ እስራኤላውያን በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በሚገኙ ቤቶች ላይ ጥቃት ካደረሱ ከአንድ ቀን በኋላ ፍልስጤማውያን ከአደጋው የተረፉትን ሲፈልጉ  

ዩኒሴፍ 'የህፃናት ግድያ እና እገታ' እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት በምህፃረ ቃል ዩኒሴፍ ተብሎ የሚጠራው ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኘውን እና ብዙ ህዝብ በሚኖርበት የጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ እስራኤል የአየር ጥቃት ካደረሰች በኋላ አከባቢው ወደ 'አስፈሪ እና አሰቃቂ' ትዕይንቶች መቀየሩን ተከትሎ ለአከባቢው ትኩረት ሰጥቶታል። ዩኒሴፍ 'የህፃናት ግድያ እና እገታ' እንዲቆም በተደጋጋሚ በመማፀን ሰብአዊ የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ የሆነው ዩኒሴፍ በጋዛ ሰርጥ ብዙ ህዝብ በሚኖርበት የጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ ጥቅምት 21, 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ሞት እና ውድመት መድረሱን በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።

መግለጫው እልቂቱን ‘አስፈሪ እና አስደንጋጭ’ በማለት የገለፀ ሲሆን፥ በ25 ቀናት ውስጥ በተካሄደው ተከታታይ የቦምብ ጥቃት ይሄኛው በካምፑ ላይ የተካሄደው ሁለተኛው ጥቃት መሆኑን እና በትንሹ 80 ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸውን የጋዛ ሆስፒታል ባለስልጣናት ገልጸዋል። የእስራኤል መከላከያ ሃይል በበኩሉ ጥቃቱ ያነጣጠረው በሃማስ አዛዦች፣ ተዋጊዎች እና ሃማስ በሚጠቀምባቸው መሰረተ ልማቶች ላይ ነው ብሏል።

ከ 3500 በላይ ህጻናት ተገድለዋል፣ ወደ 7000 የሚጠጉ ቆስለዋል

የዩኒሴፍ መግለጫ እንዳሳወቀው ባለፉት ሶስት ሳምንታት ተኩል ውስጥ እስራኤል ባደረገቻቸው የቦምብ ጥቃቶች ከ3,500 በላይ ህጻናት መሞታቸውን እና ከ6,800 በላይ ህጻናት ደግሞ መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል። ይህ ማለት በዚህ ጊዜ ውስጥ በቀን ከ 400 በላይ ህጻናት ይገደላሉ ወይም ጉዳት ይደርስባቸዋል ማለት እንደሆነ እና ይህም እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል።

ዩኒሴፍ በማከልም ዓለም አቀፉ የሰብአዊነት ህግ በግጭት ውስጥ የሚገኙትን የስደተኛ ካምፖች እና በሃገር ውስጥ ተፈናቅለው መጠልያ ጣቢያ ውስጥ የተጠለሉትን ሲቪል ህዝቦች እንዲያከብሩ እና እንዲጠብቁ እንደሚያስገድድ አስታውሷል። የዩኒሴፍ መግለጫ “ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው የመኖሪያ ሰፈሮች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የጅምላ ጥቃት እንደሆነ እና ይሄም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው” ብሏል።

የህፃናት ግድያ እና እገታ መቆም አለበት

ዩኒሴፍ በተጨማሪም “ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ከዚህ በፊት ብዙ መከራ ተቋቁመው ኖረዋል፥ እናም ከአሁን በኋላ የህፃናት ግድያ እና እገታ መቆም አለበት” ሲል ህጻናት ኢላማ መሆን እንደሌለባቸው አሳስቧል።

ይህ ጥቅምት 21, 2016 ዓ.ም. የወጣው የዩኒሴፍ መግለጫ በማጠቃለያው “በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ መሰረት ለሁሉም ግጭት ውስጥ ላሉ ወገኖች አፋጣኝ ሰብአዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የሁሉንም ህፃናት ጥበቃን ለማረጋገጥ እና ወደ ጋዛ የህይወት አድን ዕርዳታን ለማድረስ እንዲቻል ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያልተከለከለ ሰብአዊ እርዳታ ማስተላለፊያ መንገድ መኖር አለበት” ሲል የዩኒሴፍን ተደጋጋሚ ጥሪ አስተጋብቷል።

ዩኒሴፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለህጻናት ድንገተኛ የሰብአዊ እርዳታ እና የእድገት ድጋፎችን ለማቅረብ የተቋቋመ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ ነው።
 

03 November 2023, 13:19