ፈልግ

የታጋቾቹ ዘመዶች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ የታጋቾቹ ዘመዶች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ  (@FrancoPiroli)

አንድ የእስራኤላዊ ታጋች ዘመድ ‘ር.ሊ.ጳጳሳት በሥቃያችን ጊዜ ከእኛ ጋር እንደነበሩ ይሰማኛል’ አለች

መስከረም 26 ልጇን በሃማስ የተነጠቀችው ራቸል ጎልድበርግ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ከተገናኘች በኋላ “የእሳቸውን ርኅራኄ ተሰማኝ" ስትል ተናግራለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ረቡዕ ጠዋት ከሚካሄደው አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምርሆ መርሃግብር በፊት ቤተሰቦቻቸው በሃማስ ታግተው ከሚገኙ 12 ግለሰቦች ጋር ተገናኝተዋል።

የታጋቾቹ ቤተሰቦች ከብጹዕነታቸው ጋር ተገናኝተው ካወሩ በኋላ ሮም በሚገኘው ‘ኢል ፒቲግሊያኒ’ በተባለው የአይሁዳዊያን ማእከል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በቤተሰባቸው አባላት ላይ በተፈፀመው አፈና የተሰማቸውን ሀዘን እና በቅርቡ ከእነሱ ጋር የመገናኘት ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። ማይክል ሌቪ የተባለ አንድ ተናጋሪ በመግለጫው ወቅት በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ታግቶ የሚገኘው የሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ህፃን ዘመዱን አሻንጉሊት ይዞ ነበር።

 

ቡድኑ ቀደም ብሎ ማለዳ ላይ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ጋር ስለነበራቸው ቆይታም አብራርተዋል። በጊዜ እጥረት ምክንያት ሁሉም ከእሳቸው ጋር መነጋገር እንዳልቻሉ ቢገልጹም፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ታሪካቸውን በማዳመጣቸው እና ላሳዩት የርህራሄ ስሜት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከታጋች ዘመዶች ቡድን ውስጥ አንዱ የሆነው ሞሼ ሌምበርግ ቤተክርስቲያኒቱ ምን ተጨማሪ እርዳታ መስጠት እንደምትችል ተጠይቆ እንደተናገረው፥ ጳጳሱ መስከረም 26 በሃማስ ታጣቂዎች ስለተከናወኑት ድርጊቶች መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እና በዚያ አሳዛኝ ቀን የሆነውን ነገር ‘ለአለም እንዲያስታውሱ’ ጥሪውን አቅርቧል።

ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ‘ኦሰርቫቶሬ ሮማኖ’ የተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ሮቤርቶ ሴቴራ የቡድኑ አባል የሆነችውን እና ወንድ ልጇን በሃማስ ታጣቂዎች የተወሰደባትን ራቸል ጎልድበርግን አናግሯል።

ሮቤርቶ ሴቴራ፦ ራቸል፣ እየሩሳሌም ከተገናኘን ከአስር ቀን በኋላ እንደገና ተገናኝተን ለጳጳሱ የቪዲዮ መልእክት ልከሽ ነበር። በመጨረሻም አሁን ሮም መጥተሽ ከጳጳሱ ጋር ተገናኝተሽ አውርተሻል፥ ግን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ስትነጋገሪ ምን ተሰማሽ?

ራቸል ጎልድበርግ፦ ከቅዱስ አባታችን ጋር የመገናኘት እድል በማግኘቴ ታላቅ ክብር እና ምስጋና ይሰማኛል፥ በእውነት ተባርኬ ነበር። የርኅራኄው ስሜት ተሰማኝ። በሥቃያችን ወቅት አብረውን እንደነበሩ ተሰምቶኛል፥ እናም ያንን እድል በማግኘታችን በጣም እድለኛ መሆናችን ተሰምቶኛል።

ሮቤርቶ ሴቴራ፦ ከቪዲዮ መልእክትሽ ለይተውሽ ያወቁሽ ይመስልሻል?

ራቸል ጎልድበርግ፦ አይመስለኝም፥ ምናልባት በሺዎች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መልዕክቶች እንደሚደርሷቸው እገምታለሁ፥ ነገር ግን ለእኛ እና ለሰዎች ሁሉ፣ ለታጋቾች ሁሉ፣ በጋዛ ውስጥ ላሉ ሰዎች ሁሉ እንዲሁም እየተሰቃዩ ካሉት ሰዎች ጋር ያላቸው ቅርበት በደንብ ለማወቅ ችያለሁ። በዚህም ምክንያት ብዙ ተስፋ ሰጥተውኛል።

ሮቤርቶ ሴቴራ፦ ከሁለቱም ወገን ንፁሀን ተጎጂዎች እንዳሉ ጠቅሰሻል።

ራቸል ጎልድበርግ፦ በትክክል፣ በትክክል፥ እና ይህ በመሆኑ ለሁሉም ጥሩ ልብ ላላቸው ሰዎች አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ። ለቅዱስ አባታችንም በእርግጥ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ።
 

24 November 2023, 14:53