ፈልግ

ከደቡብ እስራኤል ሆኖ እንደሚታየው ከጋዛ ሰማይ ላይ የታየ የቃጠሎ ነበልባሎች ከደቡብ እስራኤል ሆኖ እንደሚታየው ከጋዛ ሰማይ ላይ የታየ የቃጠሎ ነበልባሎች  

ፕሮፌሰር አምኖን አራን፡ የሁለቱ ሃገራት የመፍትሄ ሃሳቦች አሁንም ሊቀራረቡ አልቻሉም አሉ

የለንደን ከተማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አምኖን አራን ለሎዘርቫቶሬ ሮማኖ በሰጡት ሰፊ ቃለ ምልልስ በእስራኤል እና ፍልስጤም መሃል የተከሰተው ግጭት የሁለቱ ሃገራት የጋራ መፍትሄ ብቸኛው እና አዋጭ ቢሆንም፥ አሁንም ድረስ ግን በፍጹም ሊቀራረቡ አልቻሉም ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አምኖን አራን በለንደን ከተማ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምስራቅ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፥ የቫቲካን ዕለታዊ ጋዜጣ በሆነው ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ ላይ ከሚሰራው ሮቤርቶ ፓግሊያሎኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ አዲሱ የእስራኤል-ሃማስ ግጭት እና ስለሚያስከትለው ውጤት ሰፋ ያለ ትንታኔ ሰጥተዋል።

የሁለቱም የእስራኤል እና የሃማስ አላማዎች አሁን ላለው ውዝግብ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ

በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተደገፈ የሁለቱ ሃገራት መፍትሄን አዋጭነት ተጠይቀው፥ ምንም እንኳን የመፍትሄ ሂደቱ አሁንም በጠረጴዛው ላይ ቢሆንም፣ በእስራኤል እና ፍልስጤም ውስጥ ያለው የፀጥታ እና የፖለቲካ ሁኔታዎች እስኪቀየሩ ድረስ በዚህ አካሄድ ነገሮችን መቀየር እንደማይቻል ተናግረዋል። እንደ እስራኤላዊው ምሁር ገለጻ፥ እየተካሄደ ያለው ግጭት እና የሁለቱም ማለትም የእስራኤል እና የሃማስ ዓላማዎች አሁን ላለው ግጭት አስተዋፅዖ ያደረጉ ሲሆን፥ የተኩስ አቁም ስምምነቱንም የማይቻል ያደርገዋል ብለዋል።

በቃለ መጠይቁ ላይ ፕሮፌሰር አራን እንደተናገሩት የእስራኤል ዓላማ ሃማስን እንደ ፖለቲካዊ ሃሳብ ማጥፋት ሳይሆን በተጨባጭ የሃማስን ወታደራዊ አቅም ማጥፋት ነው ብለዋል። ሆኖም ግን እስራኤል የሃማስን ወታደራዊ ሃይል በከፍተኛ ሁኔታ ማዳከም ከቻለ፥ መጨረሻ ላይ ምን ሊሆን እንደሚችል አሁንም ያልተመለሰ ጥያቄ አለ ብለዋል።

ከእስራኤል - ፍልስጤም ጦርነት በኋላ የሚከሰተው ትርምስ

ከጦርነቱ በኋላ በእስራኤል ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ነገር አስመልክቶ ፕሮፌሰር አራን እንደተናገሩት፥ የእስራኤልን ደህንነት ለማረጋገጥ በእስራኤል ማህበረሰብ ውስጥ ግጭቱ የማይቀር መሆኑን በተመለከተ ሰፊ መግባባት እንዳለ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በፖለቲካ ደረጃ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እጦት በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ መለያየት ሊፈጥር እንደሚችልም ተናግረዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን ከጦርነቱ በኋላ እንዲያስተዳድር አሜሪካ ስላቀረበችው እቅድ ተጠይቀው ፕሮፌሰር አራን ጉዳዩ እውነት ሊሆን እንደሚችል በማመን፥ ነገር ግን ከፍልስጤም ብሄራዊ መንግስት ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች፥ ለምሳሌ በዌስት ባንክ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታዎችን የመሳሰሉ ያልተፈቱ ጥያቄዎች እንዳሉም አመላክተዋል።

 በተጨማሪም ፕሮፌሰር አራን በአሁኑ ወቅት የፍልስጤም ብሄራዊ መንግስት እየተጋፈጠ ያሉትን ተግዳሮቶች ማለትም የ88 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ደካማ አመራር እንዲሁም የህጋዊነት እና የሙስና ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው፥ ሃማስ ከተዳከመ ይህንን ክፍተት መሙላት የሚችል ሌላ ተዋናይ እንደሌለ ጠቁመዋል።

በግጭቱ ውስጥ የሌሎች አገሮች ሚና

በግጭቱ ውስጥ የሌሎች ሀገራት ሚናን በተመለከተ ፕሮፌሰር አራን ከሁለቱም ወገኖች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸውን የኳታር እና ግብፅ ሽምግልና በማስታወስ፥ ዮርዳኖስን በተመለከተ የበለጠ የመከላከል አቋም ላይ ስለሆነች በዌስት ባንክ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንዳይፈነዳ ተስፋ አድርገዋል።


ከዚያም በግጭቱ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉትን ኢራን እና አጋሮቿን፣ በሊባኖስ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሂዝቦላህ እና የየመን ሁቲዎችን ጨምሮ፥ በጋዛ ግጭት ሩሲያ ከሃማስ ጎን እንደምትሰለፍ በመግለፅ ጦርነቱ ወደሌሎች ሃገራት ከተዛመት ሊያመጣ የሚችለውን መዘዝ አመላክተዋል።

በተቃራኒው ዩናይትድ ስቴትስ ጦርነቱ እንዳይራዘም በመስጋት በቀይ ባህር እና በሜዲትራኒያን ምሥራቃዊ አካባቢ ጦሯን እንዳሰማራች ከገለፁ በኋላ፥ ሳውዲ አረቢያ በበኩሏ (ከመስከረም 26ቱ የሃማስ ጥቃት በፊት ከእስራኤል ጋር የገባችውን ስምምነት እያጠናቀቀች የነበረችው) እስካሁን ድረስ ዝቅተኛ መገለጫ ቢኖራትም፥ ከግጭቱ በኋላ ለሚደረገው ስምምነት የህጋዊነት ሽፋን እና ገንዘብ ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረዋል።

የቱርኪዬን አቋም በተመለከተ ፕሮፌሰር አራን እንዳብራሩት፥ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከሃማስ ጎን እንደሚቆሙ በግልጽ በመናገራቸው ምክንያት በግጭቱ ወቅት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደማይችሉ ተናግረዋል። ነገር ግን ምንም እንኳን ኤርዶጋን ከጠ/ሚ ኔታንያሁ ተተኪ ጋር ብቻ ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ቢታወቅም፥ አንካራ እና ቴል አቪቭ የሀይል አቅርቦት እና ደህንነትን ጨምሮ የጋራ ፍላጎቶች ስላላቸው ምናልባት በመልሶ ግንባታው ሂደት ውስጥ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
 

15 November 2023, 15:36