ፈልግ

አባ ሃንስ ጆአኪም ሎህሬ ከአንድ ዓመት እስራት በኋላ ነፃ ወጥተዋል አባ ሃንስ ጆአኪም ሎህሬ ከአንድ ዓመት እስራት በኋላ ነፃ ወጥተዋል  (AFP or licensors)

ማሊ ውስጥ ታግተው የነበሩት ጀርመናዊው ሚስዮናዊ ከአንድ ዓመት ምርኮ በኋላ ነፃ መውጣታቸው ተነገረ

አባ ሃንስ-ጆአኪም ሎህሬ የተባሉት የጀርመን ተወላጅ የሆኑት ሚስዮናዊ ካህን በማሊ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ባላቸው ጽንፈኞች ታግተው ከአንድ ዓመት በኋላ ተፈተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
አባ ሃንስ-ጆአኪም ሎህሬ የተባለሉት ጀርመናዊ የአፍሪካ ሚስዮናዊ ማሊ ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ በጽንፈኞች ታስረው ከእስር ተፈተዋል። የቫቲካን ፊደስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የ66 ዓመቱ ካህን በህዳር ወር 2015 ዓ.ም. ከመጥፋታቸው በፊት በሀገሪቱ ውስጥ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ኖረዋል ተብሏል።

‘አር.ኤፍ.አይ’ የተባለው የፈረንሣይ ዜና አሰራጭ በበኩሉ የሚስዮናዊውን መፈታት ዘግቧል። በርሊን ግን በጉዳዩ ላይ እስካሁን በይፋ አስተያየት እንዳልሰጠች ተነግሯል።

መልቀቅ

ፊደስ የአባ ሃንስን ነጻ መውጣት በተመለከተ “ግልፅ ያልሆኑ” ሁኔታዎች እንዳሉ ይጠቅሳል። ባለፈው ህዳር 16, 2016 ዓ.ም. እሁድ ዕለት ከእስር የመፈታታቸው ዜና የተነገረው በማሊ መንግስት ተወካይ እና በሁለት የቤተክርስቲያን መሪዎች ነው።
የጀርመን መንግሥት በቀጥታ በድርድሩ እንደተሳተፈና ካህኑ ከተፈቱ በኋላ በልዩ በረራ ቀጥታ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉም ተነግሯል።

ጀርመን አሁንም በተባበሩት መንግስታት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ አካል የሆነ ወታደራዊ ቡድን ማሊ ውስጥ እንዳላት የሚታወቅ ሲሆን፥ በ 2014 ዓ.ም. በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተረከበው የሀገሪቱ ጦር በጠየቀው መሠረት በዓመቱ መጨረሻ የጀርመን ጦር ማሊን ለቆ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

አገልግሎት እና እገታ

በአካባቢው "ሃ-ጆ" በሚል የክብር ሥም የሚጠሩት አባ ሎህሬ ማሊ በነበሩበት የሰላሳ ዓመት ቆይታቸው፥ በሀገሪቱ ‘እስላማዊ-ክርስቲያን ምስረታ ተቋም (IFIC) ውስጥ ሰርተዋል። በተጨማሪም በሃምደላዬ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ‘የሃይማኖቶች እና የግንኙነቶች ማእከል’ ውስጥ ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል።

በካላባን ኩራ ለሚገኙ ገዳማዊያን እህቶች ማህበረሰብ መስዋዕተ ቅዳሴ ለማቅረብ እየሄዱ ባለበት ሰዓት ነው አባ ሎህሬ የተያዙት። ፊደስ የዲፕሎማቲክ እና የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፥ ካህኑን ጠልፈው የወሰዱት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ‘የእስልምና እና የሙስሊም ደጋፊ ቡድን’ (JNIM) እንደሆኑ ገልጿል።

ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በምእራብ ኒጀር ታፍኖ ተወስዶ በታህሳስ 2015 ዓ.ም. ከእስር ከተፈታው ዮርግ ላንግ ከተባለው የእርዳታ ሰራተኛው በኋላ፥ አባ ሎህሬ በሳህል ውስጥ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተለቀቁ ሁለተኛው ጀርመናዊ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

ጣሊያናዊ ጥንዶች ከነ ወንድ ልጃቸው እና አንድ ደቡብ አፍሪካዊን ጨምሮ በርካታ የውጭ ሀገር ታጋቾች አሁንም ሳህል ውስጥ ታግተው እንደሚገኙ ፊደስ ገልጿል። (ሳህል 10 ሃገራትን ማለትም ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ ሞሪታኒያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ እና ሴኔጋልን የሚያጠቃልል ክልል ነው)

28 November 2023, 13:08