ፈልግ

በቡችሽታብ ቤተሰብ የቀረቡ ፎቶዎች በቡችሽታብ ቤተሰብ የቀረቡ ፎቶዎች 

የኪቡትዝ ነዋሪዎች እገታው ከተፈፀመ ከአንድ ወር በኋላ፡ 'ልጆቻችን እንዲመለሱ እንፈልጋለን' አሉ

መስከርም 26 በሃማስ ታጣቂዎች ልጆቻቸው ከታገቱባቸው ሰዎች መካከል የአንዱ እናት የሆኑት በሃማስ ታጣቂ ቡድን የደረሰባቸው ጥቃት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ከገለፁ በኋላ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሁሉንም ታጋቾች ነፃ ለማውጣት ላደረጉት ጥሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከአንድ ወር በፊት፥ ሪሞን እና ያጌቭ ቡችሽታብ የተባሉ ባለትዳሮች የሐማስ ታጣቂዎች በኪቡትዝ መንደር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ካደረሱ በኋላ ተሰውረዋል። አሁን ባለው ሁኔታ አንፃር በጋዛ ታግተዋል ተብሎ ይታሰባል። በኪቡትዝ ውስጥ ነዋሪ የነበሩት ወ/ሮ አስቴር ቡችሽታብ የሚባሉት የታጋቹ ያጌቭ እናት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የሃማሱ ጥቃት እጅግ በጣም አስፈሪነ እንደነበረ ከገለፁ በኋላ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ታጋቾቹ እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ላሰሙት ጥሪ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

እገታ

ወ/ሮ ቡችሽታብ ዕለቱን ሲያስታውሱ “መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ ቅዳሜ (ሻባት) ቀዩ የማንቂያ ደወል ሲደወል ከእንቅልፋችን ነቃን” በማለት ተናግረዋል። ለእነሱ አዲስ ያልሆነው ደውሉ በተለምዶ የሮኬት ጥቃትን የሚያመለክት ነበር። ወ/ሮ ቡችሽታብ ይህንን ሲያብራሩ ምንም እንኳን ነዋሪዎች የማንቂያ ደውሎቹን ቢለምዱትም፥ ብዙም ሳይቆይ ይህ የተለየ መሆኑን ተገነዘቡ። የሮኬት ጥቃቶች ሲሰነዘሩ ከሚደበቁበት የደህንነት ክፍላቸው በር ውጭ በሚሰሙት ተኩስ እና የአረብኛ ተናጋሪ ድምጾች የሃማስ ታጣቂዎች ኪቡትዝ ውስጥ እንደገቡ ተግነዘቡ።

መጀመሪያ አከባቢ ላይ ወ/ሮ ቡችሽታብ እና ባለቤታቸው ከልጃቸው እና ከምራታቸው ጋር በስልክ ይገናኙ እንደነበር፥ ነገር ግን ከጥዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ምንም ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳቆሙ ገልፀዋል። ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ እና የእስራኤል ወታደሮች ኪቡትዝ ሲደርሱ፥ ወ/ሮ ቡችሽታብ “ወታደሮቹ ወደ ቤታቸው እንዲወስዱን ጠየቅናቸው” ብለዋል። ትዕይንቱንም ሲያስታውሱ “የቤቶቻችን መስኮቶች ተሰባብረዋል፣ ቤቱ በፍርስራሽ ተሞልቶ ነበር፣ የተኩስ ድምፅም ይሰማ ነበር፥ ሆኖም ግን ያጌቭ እና ሪሞን አልነበሩም። በመጨረሻም ታግተው እንደነበር ተረዳን” ብለዋል።

ታጋቾች እንዲፈቱ የቀረበ ጥሪ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጋዛ እየተካሄደ ላለው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ከማቅረባቸውም በተጨማሪ በሃማስ የተያዙት የእስራኤል ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ደጋግመው ተማጽነዋል።

ወ/ሮ ቡችሽታብ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “ብጹዕነታቸው ያቀረቡት ጥሪ ‘ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው’ በማለት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን አመስግነዋል። በማስከተልም “የጳጳሱን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ እና ጠንካራ የሞራል አቋማቸውን እናከብራለን፥ እሳቸው በዚያን አሳዛኝ ቀን ታፍነው የተወሰዱት በሰላም እንዲመለሱ በመርዳት ረገድ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ይመስለናል” ሲሉም ተናግረዋል። በመጨረሻም “ከሁሉም በላይ፥ የእኛ ጥልቅ ምኞት ልጆቻችን ወደ ቤት እንዲመለሱ እና ቤተሰቦቻችን በሰላም እንዲኖሩ ነው” በማለት አበክረው ተናግረዋል።
 

10 November 2023, 13:32