ፈልግ

የሃይማኖት መሪዎች ለዓለም አቀፍ የሃይማኖት ጉባኤ በአቡ ዳቢ ተሰብስበው የሃይማኖት መሪዎች ለዓለም አቀፍ የሃይማኖት ጉባኤ በአቡ ዳቢ ተሰብስበው 

ዓለም አቀፍ የሃይማኖይ መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁ

የዓለም ሀይማኖቶች ተወካዮች በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው COP28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የፖለቲካ መሪዎች ለአስቸኳይ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል ትርጉም ያለው እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቅ የጥሪ ሰነድ ላይ ፈርመዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአል-አዝሃር (የግብጽ ጥንታዊ ዩኒቨርሲቲ) ታላቁ ኢማም ተወካይ ፕሮፌሰር ሞሃመድ አል-ዱዌኒ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን በመወከል ጉባኤው ላይ ይተገኙት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለ COP28 ልዑካን የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ወሳኝ እርምጃ እንዲወስዱ የተላለፈው ጥሪ ላይ የፈረሙትን ወደ ሰላሳ የሚጠጉ የሃይማኖት መሪዎች ልዑካንን መርተዋል።

የአይሁድ፣ የቡድሂስት፣ የሲክ እና የሂንዱ መሪዎች ከሌሎች ዋና ዋና ባህላዊ ሃይማኖት ተወካዮች ጋር በመሆን የሃይል አቅርቦት ሽግግርን ማፋጠን፣ ምድርን መጠበቅ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ወደ መኖር የኑሮ ዘይቤ መሸጋገር እና የአየር ብክለትን የማይፈጥር የሃይል አቅርቦት እንዲኖር የሚመክር፥ በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው COP28 ኮንፍረንስ ላይ ለሚሳተፉ የፖለቲካ መሪዎች የሚሰጥ የሃይማኖት ተወካዮች ጥሪን ያካተተ ሰነድ ላይ በመፈረም ተሳትፈዋል።

ጥሪው በተጨማሪም በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን 'የሃይማኖት ድንኳን' (Faith Pavillion) በሚል በCOP28 ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ የሚቻልበትን አግባብ የሚደግፍ እና በወደፊት የCOP ኮንቬንሽኖች ላይ ለመሰባሰብ የሚቻልበትን አሰራር እንዲተገበር የሚያሳስብ ጥሪን ያካትታል። የፊርማ ስነ ስርዓቱ የተካሄደው በአቡዳቢ ከተማ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ማጠቃለያ ላይ ነው። በጉባኤው የተሳተፉ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎች ሰነዱን ከመፈረማቸው በፊት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዘንድ እንደ ብሄራዊ ዛፍ የሚታየውን የጋፍ ዛፍ በመትከል ላይ ተሳትፈዋል።

ጠንካራ መግለጫ

በሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ የጥሪውን ሰነድ ለ COP28 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ለዶክተር ሱልጣን አል ጃበር ተሰጥቷል። ዶ/ር አል ጃበር የአቡ ዳቢ የሃይማኖት መሪዎች መግለጫ ለ COP28 ስብሰባ ያለውን “ልዩ ጠቀሜታ” አጉልተው አንስተዋል። “የእናንተ የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ስብስብ ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ እና ደካማ የሆነውን ዓለማችንን ለመጠበቅ እንዲንቀሳቀሱ ያበረታታል፥ አንድ ላይ በመሆን በህብረት ያወጣችሁት መግለጫ ዓለም ላይ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስገነዝበን ነው። ይህ መግለጫ በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ መግለጫ፣ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የሃላፊነት እና የተስፋ መግለጫ ነው፥ ይህም የጋራ ለውጥ እንቅስቃሴን እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዞን ብቻ የሚያግዝ ነው” ብለዋል።

ዶ/ር አል ጃበር የሃይማኖት መሪዎች ማህበረሰባቸውን በዓለም ዙሪያ ማሰባሰብ እና ማገዝ እንዲቀጥሉ በማበረታታት፥ እሳቸውም በበኩላቸው “መልእክታችሁን በCOP28 ጉባኤ ለዓለም ለማድረስ” ቃል እገባለሁ ብለዋል።

አንድነት ለለውጥ

የክርስቲያን፣ እስልምና፣ ሂንዱይዝም፣ ቡዲዝም፣ ጃኢኒዝም እና ሌሎች በርካታ ባህላዊ ሃይማኖቶች፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ ሃይማኖቶች በዓለም አቀፍ የሃይማኖት ጉባኤ ላይ የተወከሉ ሲሆን፥ ወደ ሶስት ደርዘን የሚጠጉ ተናጋሪዎች ፍጥረትን ለመንከባከብ የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አጉልተው አንስተዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ተወካይ፣ የታላቁ ኢማም አህመድ አል ታይብ ተወካይ፣ የቁስጥንጥንያ ማኅበረ ቅዱሳን ፓትርያርክ ተወካይ እንዲሁም የሞስኮ ፓትርያርክ እና የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ተወካዮች ይገኙበታል።

ሁሉም ባህላዊ ሃይማኖቶች በመለኮት እና በፍጥረት መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚገነዘቡ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። አከባቢን የመጠበቅ የሞራል ግዴታን፣ የእግዚአብሔርን ፍጥረት መንከባከብን ጨምሮ የጋራ የሆኑ ጭብጦች በጉባኤው ተዳሰዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት አብሮ የመስራት አስፈላጊነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ አጣዳፊነት እውቅናን መስጠት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ እርምጃ የመውሰድ አስፈላጊነት ላይ በአጽንኦት መክረዋል።

ተሳታፊዎቹ ስግብግብነት እና እራስ ላይ ብቻ ማተኮርን የአካባቢ ቀውሱ መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ ሃላፊነት የተሸከሙ ሀብታም ሀገራት በአየር ንብረት ብክለት ላይ ምንም አስተዋፅኦ ባላደረጉት እና የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ድሃ ሀገራትን ለመርዳት ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የአየር ንብረት ለውጥ የዘመናችን ትልቁ ጉዳይ በመሆኑ የሚያስከትለውን አደጋ ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ተናግረዋል።

ግንዛቤን ማሳደግ

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ህዝብ የራሱ የሆነ ሀይማኖታዊ እምነት እንዳለው በመገንዘብ፥ የሀይማኖት መሪዎች በማህበረሰባቸው ውስጥ የአየር ንብረት ጉዳዮችን ግንዛቤ የማስጨበጥ ወሳኝ ሀላፊነት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

የሃይማኖት መሪዎቹም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አማኞችን ለማሰባሰብ ከፍተኛ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። ምእመናኖቻቸው በግልም ሆነ በህብረት ለጤናማ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት እና የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ማበረታታት እንዳለባቸው ብሎም የዓለም መሪዎች ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ግፊት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
 

07 November 2023, 12:50