ፈልግ

የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

በእስራኤል እና በሐማስ ጦርነት ጋዜጠኞች ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸው ተገለጸ

በእስራኤል ጦር እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በተጀመረ ጦርነት፥ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በሚገኙ መሠረተ ልማቶች ላይ ስትፈጽም በቆየችው ጥቃት 39 ጋዜጠኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተረጋግጧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች እስራኤል በጋዛ ከተማ የምትፈጽመውን የምድር ጥቃት፣ አውዳሚ የአየር ድብደባ፣ የመገናኛ፣ የመብራት እና የውሃ መስመሮች መቋረጥን በመቃወም ግጭቱን ለመዘገብ በሚሞክሩበት ወቅት ከፍተኛ ስጋት ተጋርጦባቸዋል ተብሏል።

ነፃ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) እንደገለጸው፥ መረጃን መሰብሰብ ከጀመረበት ማለትም ከ1984 ዓ. ም. ወዲህ በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች ላይ ይደርስ ከነበረው ጥቃት ባለፈው ወር የተመዘገበው እጅግ የከፋ እንደ ነበር አስታውቋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ወዲህ 39 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል 34 ፍልስጤማዊያን፣ 4 እስራኤላዊያን እና 1 ሊባኖሳዊ መሆናቸው ሲታወቅ፣ በተጨማሪም 8 ጋዜጠኞች መቁሰላቸው፣ 3ቱ መሰወራቸው እና 9ኙ መታሰራቸው ተዘግቧል።

ግድያ፣ እገታ፣ እስራት፣ ጉዳት እና ዛቻ ደርሶባቸዋል

አንድ ፍልስጤማዊ ዘጋቢ ከሌሎች 42 የቤተሰብ አባላት ጋር መገደሉን ማክሰኞ ጥቅምት 27/2016 ዓ. ም. የወጣው ዜና አስታውቋል። ዘጋቢው ይሠራበት የነበረው ዋፋ የተሰኘ የዜና ወኪል እንደገለፀው፥ መሐመድ አቡ ሀሲራ የተገደለው እስራኤል ጋዛ ከተማ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት እንደነበር አስታውቋል።

የሞቱት ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች፥ የሐማስ ታጣቂዎች እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ወዲህ በጋዛ እና በዌስት ባንክ ከተገደሉት 11,000 ሰዎች መካከል እንደሚገኙ ነፃ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) አስታውቆ፥ ኮሚቴው በተጨማሪም ሌሎች ጋዜጠኞች መገደላቸውን፣ መጥፋታቸውን፣ መታሰራቸውን፣ መጎዳታቸውን ወይም ዛቻዎችን እና በመገናኛ ብዙሃን ጽሕፈት ቤቶች እና በጋዜጠኞች መኖሪያ ቤቶች ላይ ስለደረሱ ጉዳቶች ብዙ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶችን እየመረመረ እንደሚገኝ ገልጿል።

ሮይተርስ የዜና ምንጭ ጥቅምት 16/2016 ዓ. ም. እንደዘገበው፥ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) ለዜና ወኪሉ እና ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ፥ ጋዜጠኞቻቸው በእስራኤል ጥቃት እንደማይደርስ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ በኋላ በሰጠው ማሳሰቢያ፥ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ለሚሠሩ ጋዜጠኞቻቸው የደኅንነት ዋስትና እንደማይሰጥ ገልጿል።

ሲቪሎች ጠቃሚ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ

ነፃ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) በመግለጫው፥ “ጋዜጠኞች በችግር ጊዜ ጠቃሚ ሥራ የሚሠሩ ሲቪሎች በመሆናቸው በተፋላሚ ወገኖች ሊጠቁ አይገባም” ሲል አፅንዖት ሰጥቷል። በአካባቢው ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች ግጭቱን ለመዘገብ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸውን እና "በተለይ ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መስዋዕትነት መክፈላቸውን፣ እየከፈሉ መሆናቸውን እና ትልቅ አደጋ እንደሚደርስባቸው አስታውቋል። ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ባልደረቦቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና የሚዲያ ንብረቶቻቸውን ማጣታቸውን እና አስተማማኝ መሸሸጊያ ወይም ማምለጫ መንገድ በሌለበት ወቅትም ለደህንነታቸው በመስጋት መሰደዳቸውን ነፃ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲፒጄ) አስታውቋል። ኮሚቴው ድረ-ገጹን በየጊዜው በማደስ የተገደሉ፣ የተጎዱ ወይም የጠፉ ጋዜጠኞች ስም ዝርዝር ዘወትር ይፋ ያደርጋል።

ታማኝ ዘገባዎችን ማቅረብ

ይህ በእንዲህ እንዳለ እውነትን ገሃድ ለማድረግ በእስራኤል ጦር በተከበበች ጋዛ ውስጥ ምን እየሆነ እንዳለ ለዓለም መናገር አስፈላጊ ሆኖ ሳለ፥ በአሥራዎቹ ውስጥ የሚገኝ አንድ አዳጊ፥ “ቲክ ቶክ”ን ወደ መሳሰሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ፊቱን በመዞር የዕለቱን ዘገባ በማጠናቀር ለአድማጭ ተመልካች ሲያጋራ ተስተውሏል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በእስራኤል በተያዘች ዌስት ባንክ ውስጥ በሚገኝ ጄኒን የስደተኞች ካምፕ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት፥ ሰማያዊ የጋዜጠኛ መለያ ጃኬት ለብሳ ስትዘግብ ሳለ በእስራኤል ወታደር የተገደለች ፍልስጤማዊት አሜሪካዊት ጋዜጠኛ “የሺሪን አቡ አሌህ ልጅ” ሲል እራሱን ጠርቷል። አዳጊው ለተመልካቾቹ ዘገባውን በሚያቀርብበት ወቅት ከጀርባው የቦምብ ድብደባ እንደሚሰማ እና የእስራኤል ሚሳኤሎች ከጭንቅላቱ በላይ ሰማይ ላይ ሲንጫጩ ታይተዋል።

 

09 November 2023, 14:29