ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዳኛ መሐመድ አብዱልሰላም ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዳኛ መሐመድ አብዱልሰላም ጋር 

የሃይማኖት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና አላቸው ተባለ

የሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ዳኛ መሀመድ አብደልሰላም ከ COP28 (የ2023 የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ) ጉባኤ በፊት በአቡ ዳቢ በተካሄደው የዓለም አቀፍ ሃይማኖቶች ጉባኤ ላይ የሃይማኖት መሪዎች ያላቸውን ተፅእኖ እና የአየር ንብረት እርምጃን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመምራት ረገድ ያላቸውን ሚና አጉልተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዚህ ሳምንት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ አቡ ዳቢ ከተማ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች ጉባኤ “የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ጎጂ ተጽዕኖ’ እና ‘ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል የሀይማኖት መሪዎች ማህበረሰባቸውን በማስተባበር የሚጫወቱትን ሚና’ ላይ በማጉላት ውይይት ያደርጋል” በማለት የሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ዳኛ መሀመድ አብደልሰላም ተናግረዋል።

ዳኛ አብደልሰላም በሚቀጥለው ወር ከሚካሄደው የ COP28 ስብሰባ በፊት ከጥቅምት 26-27, 2016 ዓ.ም. ድረስ ስለሚካሄደው የዓለምአቀፍ የሃይማኖቶች ጉባኤ አጀንዳዎችን ለማብራራት ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ለአየር ንብረት እርምጃ የሃይማኖት ተቋማት አስተዋፅኦ

በአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ላይ የሚወያየው የዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ ‘የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ የተለያዩ እምነቶች እና የእምነት መሪዎች ያላቸውን ራዕይ እና አስተዋፅኦ ለዓለም ለማሳየት’ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ዋና ዋና የሀይማኖት መሪዎችን ያሰባስባል ሲሉ ዳኛ አብደልሰላም አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ “በዘመናችን ካሉት በጣም አደገኛ ቀውሶች አንዱ” መሆኑን ማወቁ የሃይማኖት መሪዎችን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተጎዱ የማኅበረሰቦች ተወካዮችን እና አማኝ ያልሆኑትን እንኳን ለማሰባሰብ ጅምር ተነሳሽነትን ሰጥቷል። በጉባኤውም በአንድ ላይ ለማሰላሰል እና ለመወያየት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ላይ አንድ ወጥ የሆነ የጥሪ መልዕክት ለማስተላለፍ እና ይህንን በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ዓለም አቀፋዊ ስጋት ለመቅረፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

የሃይማኖት መሪዎች ሚና

ዳኛ አብደልሰላም “በዓለም ዙሪያ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች እና የእምነት መሪዎች እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ትልቅ ተጽእኖ መፍጠር ይችላሉ። በዓለም ዙሪያ የአየር ንብረት እርምጃዎችን በመምራት ረገድ በጣም ጠቃሚ ሚና አላቸው” ካሉ በኋላ “በትክክል የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ ስጋት ስለሆነ የጋራ እርምጃ፣ ወጥ የሆነ አቋም እና በሁሉም ማህበረሰቦች መካከል በተለይም በእምነት መሪዎች መካከል አንድነት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የሃይማኖት መሪዎች አወንታዊ የአየር ንብረት እርምጃዎችን በተለይም በየሃይማኖት ማህበረሰቦቻቸው መካከል ግንዛቤን የማሳደግ እና በሰብአዊነት ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም ሰብአዊነትን በሰው ልጅ ተግባራት ላይ የመጀመሪያው አጀንዳ የማድረግ ችሎታን ለማሳደግ ሊወስዷቸው የሚችሏቸውን ተግባራት ገልጸዋል። ምክንያቱም ደግሞ ይላሉ አብደልሰላም “በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰብአዊ ማህበረሰብ ፍላጎቶች ቅድሚያ ስንሰጥ ይህንን የአየር ንብረት ቀውስ ለመፍታት እና የተሻሉ ግቦች ላይ መድረስ እንችላለን” በማለት ገልፀዋል።
ዳኛ አብደልሰላም በማከልም “ሁሉም ሃይማኖቶች አካባቢያችንን እና ምድራችንን እንድንከባከብ ሁል ጊዜ ጥሪያቸውን ያሰማሉ፥ ምክንያቱም ሁሉም ሃይማኖቶች “ምድራችንን የመጠበቅ ጽንሰ-ሀሳብ እና ለጋራ ቤታችን እንክብካቤን ማሳየትን አስተምርሆ ስለሚጋሩ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ይላሉ ዳኛ አብደልሰላም “የእምነት መሪዎች ማህበረሰቡን የመምራት እና ቅድሚያውን ለመውሰድ ብሎም ከዚህ ዓለም-አቀፋዊ ስጋት ለመውጣት አንድነታቸውን ለማሳየት እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ አዋጭ የሆነ ቅርስ የመተው ምሳሌን ለማሳየት ‘ስነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ ሃላፊነት እና ግዴታ’ አለባቸው” ብለዋል።

ጳጳሱ እና ታላቁ ኢማም

ዳኛ አብደልሰላም በመቀጠልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የአል-አዝሃር ታላቅ ኢማም የሆኑት አህመድ አል ጣይብ የሃይማኖት መሪዎች መሆናቸውን ጠቁመው “በዓለም አቀፍ ደረጃ ለብዙ የእምነት መሪዎች በሃይማኖቶች መካከል ውይይት እንዲደረግ በማመቻቸት ብቻ ሳይሆን በየሃይማኖታቸው ማህበረሰቦች መካከል እውነተኛ አጋርነት በመፍጠር አበረታች ምሳሌ እና አርአያነት” ያሳዩ ናቸው በማለት ሁለቱን የሃይማኖት አባቶች ገልፀዋቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ አባቶች በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች መሪዎችን እና የሀይማኖት አባቶችን የሰው ልጆችን ሁሉ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ያስችላቸው ዘንድ ወዳጅነትን በማጎልበት እንዲሁም በመቀራረብ እና በመተጋገዝ በጋራ በመስራት ላይ እንዲሳተፉ አነሳስተዋል ብለዋል።

በሰብአዊ ወንድማማችነት እና በሌሎች ውጥኖች ላይ የወጣውን ሰነድ ተከትሎ “በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚወያየው የዓለም አቀፍ እምነት መሪዎች ስብሰባም የእነዚህ አባቶች ‘የጋራ ተግባራቸው’ ውጤት ነው ካሉ በኋላ “ይህንን ተነሳሽነት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሁሉንም የእምነት እና ባህላዊ መሪዎች በአንድነት ለማሰብ፣ ለማሰላሰል፣ ራዕያቸውን ለማካፈል እና የዓለም አቀፍ እምነት መሪዎችን መልእክት ለ COP28 ጉባኤ ለሚሰበሰቡት የፖለቲካ መሪዎች ለማድረስ የሚቻልበት ዓለም አቀፍ መድረክ እንዲሆን ደግፈዋል” ብለዋል።

ዳኛ አብደልሰላም በመቀጠል “ይህ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና በታላቁ ኢማም መካከል የተደረገው ጉዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውነተኛ አርአያነትን አሳይቷል፥ ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስ ምርምር ማህበረሰብ ዘንድ በጥሩ ሁኔታ አልተንጸባረቀም ወይም ትኩረት አልተሰጠውም ብዬ አምናለሁ፡ ምክንያቱም ይህ ክስተት ሊጠናና ሊታተም ይገባዋል ምክንያቱም የሰው ልጅን ሁሉ ለማዳን ይረዳልና” ብለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በ COP28 መገኘት ልዩ ፣ ያልተለመደ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በ COP28 ስብሰባ በአካል ለመገኘት መወሰናቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ዳኛ አብደልሰላም “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ተሳትፎ ልዩ፣ ያልተለመደ እና በ COP ኮንፈረንስ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። አክለውም “ብጹዕነታቸው በጉዞአቸው መጨረሻ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን መዋጋት ጀምረዋል” ብለዋል።

በተጨማሪም ከ COP28 ኮንፍረንስ የሚጠበቀው ውጤት የጳጳሱ ድጋፍ ምልክት ነው ብለዋል። እናም “ይህኛው የ COP ኮንፍረንስ ምዕራፍ በአየር ንብረት ለውጥ እና በአየር ንብረት እርምጃ ላይ ከተደረጉት ቀደምት ኮንፈረንሶች የተለየ ይሆናል” ብለዋል።

ዳኛ አብደልሰላም ሲያጠቃልሉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ COP 28 ላይ መገኘት “ለእሳቸው የአየር ንብረት ቀውስ ጉዳይ ምን ያክል አጣዳፊ ጉዳይ እንደሆነ እንደሚያሳይ እና COP28 ያስገኛል ብለን ተስፋ የምናደርጋቸው ተጨባጭ ውጤቶች አስፈላጊነትን ያሳያል” ብለዋል።
 

06 November 2023, 14:47