ፈልግ

የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በካቡል  የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በካቡል   (ANSA)

የዓለም የፖሊዮ ቀን፡ ዩኒሴፍ የቫይረሱን ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ በ99 በመቶ ቀንሻለሁ አለ

በዓለም የፖሊዮ ቀን ዩኒሴፍ ከ2.5 ቢሊየን በላይ ህፃናት የፖሊዮ ክትባቱን መውሰዳቸውን ገልፆ ይህም ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ የበሽታውን ስርጭት 99 በመቶ መቆጣጠር እንደቻለ ይፋ አድርጓል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቅምት 13, 2016 ዓ.ም. በተከበረው በዓለም የፖሊዮ ቀን ላይ ዩኒሴፍ እንደገለፀው “በወረርሽኝ፣ በግጭት፣ በአየር ንብረት አደጋዎች፣ መፈናቀል እና እየጨመረ በመጣው ስለክትባቶቹ የሚነገሩ የተሳሳቱ መረጃዎች ምክንያት አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ክትባቱን አልተከተቡም” ሲል ለጉዳዩ አፅንዖት ሰጥቶታል።

           “አሁን የተገኘው ውጤት እድገት ደካማ ነው እናም ትኩረትን ማጣት ዬለብንም”
የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረት የፖሊዮን በሽታን ከዓለማችን ላይ ለማስወገድ የሚወጣው ገንዘብ በዚህ ክፍለ ዘመን ቫይረሱን ለመቆጣጠር እና ወረርሽኙን ለመከላከል ተብሎ ከሚወጣውጋር ሲነፃፀር 33.1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን የጤና በጀቶችን ሊቆጥብ እንደሚችል ተገልጿል።

በአፍሪካ እና በእስያ ያሉ ተጨማሪ ጉዳዮች

“ፖሊዮ በአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን እንዲሁም በአፍሪካ እና እስያ ውስጥ ባሉ ከሃያ በላይ ሀገራት ህጻናትን አካለ ስንኩላን እያደረገ ነው” ሲል ዩኒሴፍ ተናግሯል። እነዚህ አካባቢዎች የፖሊዮ ቫይረስ አሁንም የተስፋፋባቸውና እየተስፋፋ ያሉባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ኤጀንሲው አጽንኦት ሰጥቷል። ከእነዚህ ሕጻናት መካከል ብዙዎቹ ሕይወት አድን የሕክምና እንክብካቤ እና የክትባት አገልግሎት በማይያገኙባቸው በጣም ድሆች እና በጣም የተገለሉ ሰፈሮች ውስጥ ይኖራሉ።

ዩኒሴፍ ፖሊዮን ለማጥፋት ከሌሎች ተቋማት ጋር ይተባበራል

ዩኒሴፍ እንደገለጸው ከመንግስታት፣ ከአጋሮች እና ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመተባበር “በዓለም ዙሪያ ፖሊዮን ለማጥፋት በየዓመቱ ከ400 ሚሊዮን በላይ ህጻናትን የፖሊዮ ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል” ብሏል።
በተጨማሪም “እነዚህ አጋር ድርጅቶች አገሮች ደህንነቱ የተጠበቀ እና በቂ መጠን ያለው የፖሊዮ ክትባት እንዲያገኙ ለማድረግ የቁጥጥር አስተዳደር እና ሎጂስቲክስን ጨምሮ 1 ቢሊዮን የፖሊዮ ክትባቶችን በየዓመቱ ይሰጣሉ” ሲል ዩኒሴፍ ገልጿል።

ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚያትትው ከሆነ “ፖሊዮን የማጥፋትን ውጤት ካልተሳካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታው እንደገና እንዲያንሰራራ ሊያደርግ ይችላል” ብሏል። ይህ ሊሆን የሚችለው አዳዲስ የፖሊዮ ጉዳዮች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር እና የፖሊዮ ቫይረስ ልዩ ልዩ ወረርሽኞች በመስፋፋት ነው ብለዋል ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውጤት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሠላሳ ዓመታት ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ የክትባት ስርጭት እንዲቀንስ አድርጓል። ይህንንም በማስመልከት ድርጅቱ “በወረርሽኙ ወቅት በፖሊዮ፣ በኩፍኝ እና በሌሎች የተለመዱ በሽታዎች ላይ ያልተከተቡ ህጻናትን ለመድረስ መንግስታት በአፋጣኝ ኢንቨስት ማድረግ አለባቸው” ብሏል።

ፖሊዮ መወገድ አለበት

የፖሊዮ በሽታን ማጥፋት ክትባቶች እንደሚሰሩ አንዱ ማሳያ እንደሚሆን እና ለጤና ዘላቂ ልማት ግቦች ትልቅ ምዕራፍ እንደሚሆን፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ለሁሉም ህፃናት ትልቅ እና ታሪካዊ ድል ነው ተብሏል።  “ፖሊዮን ስናስወግድ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፈንጣጣ በመቀጠል ከፕላኔቷ ላይ የሚጠፋው ሁለተኛው በሽታ ብቻ ነው” ሲል ዩኒሴፍ ገልጿል።

የፖሊዮ ቫይረስ ምንም አይነት ጂኦግራፊያዊ ወሰን እንደማይገድበው ዩኒሴፍ ያረጋገጠ ሲሆን፥ ከማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ እስራኤል፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ከመሳሰሉ ለአስርት ዓመታት ከፖሊዮ ነፃ በሆነባቸው ሀገራት እንኳን ህጻናት ላይ በቀላሉ ሊዛመትና ሽባ ሊያደርግ እንደሚችል አመላክቷል።  ለፖሊዮ ቫይረስ ሀገራዊ ድንበሮች ምንም ትርጉም የለውም። ዩኒሴፍ ይሄን አስመልክቶ “ፖሊዮ በየትኛውም ቦታ እስካለ ድረስ በዓለም ላይ ላሉ ህጻናት ስጋት ይሆናል” ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ የፖሊዮ በሽታን ለማስወገድ ቀሪዎቹን መሰናክሎች በመቅረፍ ህጻናትን በክትባት ሊጠፉ ከሚችሉ በሽታዎች እና ወደፊት ከሚመጡ ወረርሽኞች መጠበቅ እንደሚቻል ያለውን እምነት ገልጿል።

በመሆኑም ዩኒሴፍ የሀገር መሪዎች ህፃናት የልጅነት ክትባት እንዲያገኙ እና ለህጻናት ቅድሚያ በመስጠት የፖሊዮ በሽታን ማጥፋት እንዲቻል ለጋሾች እና አጋሮቻቸው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
 

25 October 2023, 12:19