ፈልግ

በደቡባዊ ጋዝ ራፋህ የእስራኤል የአየር ጥቃት ተከትሎ ፍልስጤማውያን ህይወት ለማዳን የፈራረሰውን ህንፃ ሲቆፍሩ በደቡባዊ ጋዝ ራፋህ የእስራኤል የአየር ጥቃት ተከትሎ ፍልስጤማውያን ህይወት ለማዳን የፈራረሰውን ህንፃ ሲቆፍሩ   (AFP or licensors)

በጋዛ ውስጥ ለሞቱ ሰዎች መቅበሪያ የሚሆን የሬሳ መገነዣዎች እጥረት እንደተከሰተ ተነገረ

ከ 10 ቀናት በፊት የእስራኤል ድንበርን ጥሶ የገባውን የሐማስን አመራር ለማጥፋት ከሚጠበቀው የእስራኤል ወረራ በፊት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጋዛ ሰርጥ በኩል ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል ። በዮርዳኖስ አቅራቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ (UNRWA) የሰው ሃይል ዳይሬክተር በጋዛ ስላለው አስከፊ ሰብአዊ ሁኔታዎች በመግለጽ የሰብአዊነት ህግ እንዲከበር ተማጽነዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል ወታደሮች በአሜሪካ የጦር መርከቦች እየተደገፉ ሰኞ ዕለት እራሳቸውን በግጭቱ አከባቢ ድንበር ላይ በማስፈር እና እስራኤል አሸባሪ ቡድኑን ለመበተን ሰፊ ዘመቻ ነው ያለችውን ለመተግበር የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ ጥፋት ሊያፋጥን እንደሚችል የእርዳታ ቡድኖች ያስጠነቅቃሉ።
ለሳምንት የዘለቀው የማያቋርጥ የአየር ድብደባ በጋዛ ከተማ እና በሲሪፕ ውስጥ ያሉ ሰፈሮችን ቢያፈራርስም ወደ እስራኤል የሚተኮሰውን የሃማስ ታጣቂዎችን ሮኬቶች ግን ማስቆም አልቻለም። በግጭቱ እስካሁን ከ4,000 በላይ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል። መሄጃ ያጡት የጋዛ ነዋሪዎች የሚሸሹበት ምንም አስተማማኝ ቦታ እንደሌለ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ የሰው ሃይል ዳይሬክተር የሆኑት አንቶኒኖ ብሩሳ ለቫቲካን ረዲዮ እንደተናገሩት በጋዛ ቢያንስ 14 የድርጅቱ ሰራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያዎች በቦምብ ተደብድበዋል፣ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በዮርዳኖስ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት በቅርብ ምስራቅ የሚገኙ የፍልስጤም ስደተኞች ጋዛ ስለሚገኘው ቢሮአቸው የሚያውቁት ነገር ቢኖር ሙሉ በሙሉ መውደሙን እና በውስጡ የነበሩት የተለያዩ መዛግብቶች በእሳት መቃጠሉን ነው የተናገሩት።
ብሩሳ አክለውም ልክ በሚሊዮን እንደሚቆጠሩት ሌሎች የጋዛ ነዋሪዎች ሁሉ የድርጅታቸው የሰው ሃይል ሰራተኞችም ወደ ደቡብ መዘዋወራቸውን ገልፀው ስለደህንነታቸው ሲናገሩ “ለመገናኘት አስቸጋሪ ቢሆንም አንዳንዶቹ ደህና እንደሆኑ እናውቃለን” ብለዋል።

መብራት፣ ውሃ፣ ነዳጅ አለመኖሩን እና ከአንድ ሳምንት በላይ ማስቆጠሩን ሲያረጋግጡ ፥ ስልካቸውን ቻርጅ ማድረግ አዳጋች እንደሆነና በቦምብ ፍንዳታው ወቅት ወደ ውጪ ለመውጣትም በጣም እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል።
በጋዛ የሚገኙ 12 ዓለም አቀፍ የድርጅቱ ሰራተኞች ተቋሙ ሁለት ዓበይት ስራዎችን ወደ ሚሰራበት ወደ ደቡብ ማዛወር መቻላቸውን እና እዛም የሚገኙት መጠልያዎች እና መሠረተ ልማቶቹ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ተጨናንቀው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
“በአሁኑ ጊዜ ለዓለም አቀፍ ሰራተኞቻችን ለአንድ ሰው በቀን አንድ ሊትር ውሃ ይሰጣቸዋል” በማለት ፥ ይህንንም በማግኝታቸው ዕድለኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ምክንያቱም አብዛኞቹ የተፈናቀሉ ሰዎች አንድ ሊትሯንም እንኳን ማግኘት አይችሉምና ብለዋል።
አቶ ብሩሳ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን የተነፈጉበትን ሁኔታ ሲገልጹ፥ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስቸኳይ የሆነው ነገር የመጠጥ ውሃ ችግር ነው ብለዋል። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስታቱ ድርጅት ህንፃዎች በአየር ድብደባ መመታታቸውን አንስተዋል።

ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ

“የተባበሩት መንግስታት ባንዲራ ያላቸው እና ብዙ ሰዎች ከቦምብ ጥቃት ለመከላከል የተጠለሉባቸው ሕንፃዎች ሰዎች ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸው እና በቦምብ መመታታቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው” ብለዋል ሃላፊው።
“አሁን በጣም የሚያስጨንቀን ነገር በሽተኞች ሆስፒታሎችን እንኳን ለቀው እንዲወጡ መደረጉና ይህም ከሞት ፍርድ ጋር የሚያመሳስለው ነገር በሽተኛ ከሆስፒታል መውጣት እንደማይችል ጠንቅቀን ስለምናውቅ ነው” ካሉ በኋላ ፥ “ለመውለድ የተቃረቡ ነፍሰ ጡር እናቶች አሉ፣በቦምብ ጥቃቱ የተጎዱ በጣም የታመሙ እና መቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎች አሉ” በማለት ስለ ጉዳዩ አሳሳቢነት ገልፀዋል። ብሩሳ በመቀጠል ዶክተሮቹ “ዬትም አንንቀሳቀስም፣ ታካሚዎቻችንን ትተን ዬትም አንሄድም፣ ከእነሱ ጋር እንሞታለን” ማለታቸውንም ተናግረዋል።

                        “ታካሚዎቻችንን ትተን ዬትም አንሄድም፣ ከእነሱ ጋር እንሞታለን”

ከጋዛ የመጡ መልዕክቶች

የሰው ሃይል ስራ አስኪያጁ በጋዛ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ የአካባቢው ሰራተኞች ስለተቀበሉት አስደናቂ መልእክት ሲናገሩ ፥ አንዲት ሴት ይህ የመጨረሻ መልእክቷ እንደሆነ በመግለፅ እና እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ በሕይወት እኖራለሁ ብላ እንደማትጠብቅ በመግለጽ መልዕክት ፃፈች። ሴትዬዋም
በጋዛ ከተማ መካከል እንደነበረች እና 'ወደ ሌላ ቦታ መሄድ እንደማትችል’፣ ምክንያቷም አዛውንት ወላጆቿን ትታ መሄድ እንደማትችል፣ ከትናንሽ ልጆቿ እና ከዘመዶቿ ጋር መንቀሳቀስ እንደማትችል፣ ግን ደግሞ ይህ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ስምንተኛው ድንገተኛ አደጋ እንደሆነ እና ይህ ሁሉ እንደሰለቻቸው’ የሚገልጽ መልዕክት ጽፋለች።
“ወደ ደቡብ ለማምለጥ ከመሞከር ይልቅ በክብር መሞትን እንመርጣለን” ይላል መልዕክቷ መጨረሻ ላይ።

                       “በክብር መሞትን እንመርጣለን”

አቶ ብሩሳ አክለውም ‘እየተቀበልናቸው ያሉ መልእክቶች ስለ ድካም፣ ፍርሃት እና መታከት ይናገራሉ። ማናችንም ብንሆን “የቦምብ ጥቃቱን ለማስቆም እንደማይሳካልን” አውቀው ጸሎትን ብቻ እንድናረግላቸው ይጠይቃሉ’ ብለዋል።
መልዕክቶቹ “የምንፈልገውን ውሃ፣ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁስ በማግኘቱ ረገድ እንኳን አልተሳካላችሁም ፣ ስለሆነም ቢያንስ ይህ እንዲያበቃልን ፣ በተቻለ ፍጥነት እንድንሞት ፣ ለረጅም ስቃይ እንዳንጋለጥ ጸልዩልን” ይላሉ።
አቶ ብሩሳ በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ውስጥ ምንም ዓይነት አስተማማኝ ቦታ እንደሌለ በማረጋገጥ ፥ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ 14 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ ሰራተኞች መገደላቸውን እና ቁጥሩ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። እንደ አለመታደል ሆኖ ማንኛውንም መረጃ ማረጋገጥ እንደማይቻል አክለዋል ። እኛ የምናውቀው ነገር ቢኖር እኛ ያቋቋምናቸው የህክምና ማእከል ፣ ትምህርት ቤቶች ፣ የእርዳታ እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ተጎድተዋል ፣ ወድመዋል፣ ካሁን በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት አይሰጡም ብለዋል።
ብሩሳ ከጠቅላላው የጋዛ ህዝብ ግማሽ ያህሉ ማለትም ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች አሁን ላይ ተፈናቅለዋል ። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት 600,000 የሚሆኑ ተፈናቃዮች በመሃከለኛ እና በደቡብ በጋዛ ሰርጥ፥ ካን ዮኒስ እና ራፋህ ውስጥ እንደሚገኙ አብራርተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 400,000 ያህሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ያሉ ሲሆን ተቋሙም ፍላጎታቸውን ለማሟላት እየታገለ ይገኛል።
ከብዛታቸው የተነሳ በጣም በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፥ምንም አይነት የስነ-ልቦና ድጋፍም ሆነ ዕርዳታ ለመስጠት እንኳን የማይታሰብ ነው። ብዙ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት ወይም መከላከል ባለመቻላቸው ማዘናቸውን እና መበሳጨታቸውን ገልጸዋል ።
አከባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ በተሰጠበት ወቅት 160,000 ተፈናቃዮች የተወሰኑ የአደጋ ጊዜ መጠለያዎችን ጨምሮ በ 57 የተቋማቸው ግቢዎች ውስጥ ተጠልለው እንደነበር በመግለፅ ፥ “አሁን ቀነ ገደቡ አልፏል ፥ ምን እንደደረሰባቸው አናውቅም” ብለዋል።

በጋዛ ውስጥ ለሞቱ ሰዎች የሚሆኑ በቂ መገነዣ ቦርሳዎች ዬሉም

አቶ ብሩሳ እንዳሉት “እኛ የምናውቀው በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ውስጥ ለሞቱ ሰዎች መቅበሪያ የሚሆኑ በቂ የመገንዣ ቦርሳዎች አለመኖራቸውን ነው። እነዚህን ሰዎች እንዴት እንደሚቀብሩ እንኳን ስለማያውቁ በሽታዎች በፍጥነት ሊሰራጩ ይችላሉ ፥ ይህ በእርግጥ የንፁህ ውሃ እጦትም ያካትታል” ብለዋል።

ጥሪ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ የሰው ኃብት ሃላፊ በጣም አስቸኳይ ጥሪ ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ፥ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች እንዲገቡ በግብፅ በኩል ያለው የራፋህ ድንበር እንዲከፈት ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደመሆናችን መጠን ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋት እና የሲቪሎች ጥበቃን እናበረታታለን፡ “በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሰብአዊነት እንድንቆይ እንጠይቃለን” ብለዋል።
የፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ሌሎች ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በ9 ቀናት ውስጥ 2,329 ፍልስጤማውያን በጋዛ ተገድለዋል ሲሉ አቶ ብሩሳ ተናግረዋል። ነገር ግን እነዚህን አሃዞች በአሁኑ ሰዓት አለመጨመራቸውን ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል።
እንዲሁም “የእኛ አቤቱታ ሆስፒታሎች እንዲከበሩ ነው” ካሉ በኋላ፥ በጦርነት ጊዜ የሰብአዊነት ህግ መከበር እንዳለበት ጠቁመው፥ “ህሙማንን ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ መጠየቅ አትችልም ምክንያቱም ደግሞ ለቀው መውጣት ስለማይችሉ ነው” ብለዋል።
ለዚህም ነው ዶክተሮቹ ከአከባቢው የመልቀቂያ ትዕዛዞችን ህሙማኑ ላይ የተፈረደ የሞት ፍርድ እንደሆነ አድርገው የገለፁት፥ ለዚህም ነው ‘እባካችሁ በቶሎ ጨርሱን፣ በተቻለ ፍጥነት እንድንሞት አግዙን፣ ነገር ግን መከራውን አታራዝሙብን' የሚሉት መልዕክቶች የደረሱን ብለዋል አቶ አንቶኒኖ ብሩሳ።
 

17 October 2023, 21:46