ፈልግ

ፍልስጤማውያን ተፈናቅለው በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ራፋህ  የተባበሩት መንግስታት መጠለያ ውስጥ ላሉት ምግብ እያዘጋጁ ፍልስጤማውያን ተፈናቅለው በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ራፋህ የተባበሩት መንግስታት መጠለያ ውስጥ ላሉት ምግብ እያዘጋጁ   (AFP or licensors)

የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች ወደ ጋዛ ያልተገደበ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲገባ አሳሰቡ

የተባበሩት መግስታት የህፃናት ፈንድ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከተባበሩት መንግስታት ልማት ድርጅት (UNDP)፣ ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA)፣ ከዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) እና ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ጋር በመሆን በመላው ጋዛ የብዙዎቹን ህይወት ለማዳን በተለይም በጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ህጻናትን ለማትረፍ ሲባል ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤል ጋዛን እየከበበች ባለችበት እና በሃማስ የታገቱት ሰዎች ጉዳይ እልባት ባላገኘበት በዚህ ቀዉሱ እየተስፋፋ በመጣበት አስቸጋሪ ወቅት ዩኒሴፍ እና ሌሎች አራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ህይወትን ለመታደግ እና ተጨማሪ የሰው ልጆችን ስቃይ ለመቀነስ በመላው ጋዛ ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት አቅርቦት እንዲደርስ እና ሰብአዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የመጀመሪያ ግን ውስን የሆነው ከ44,000 በላይ የሚሆኑ የታሸጉ የመጠጥ ውሃን ጨምሮ ከተባበሩት መንግስታት እና ከግብፅ ቀይ ጨረቃ የተላኩ የአደጋ ጊዜ አቅርቦቶች በጥቅምት 10, 2016 ዓ.ም. በራፋህ መሻገሪያ በኩል ወደ ጋዛ ገብቷል። ይህም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩት ከውሃ፣ ከምግብ፣ ከመድሀኒት፣ ከነዳጅ እና ከሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ለተቆራረጡ ንፁሀን ዜጎች ህይወት አድን ዕርዳታ እንደሆነ ተስፋ ተጥሎበታል። የመንግሥታቱ ድርጅት የእርዳታ አግልግሎት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ እንዳሉት 2.1 ሚሊዮን የሚሆኑ የጋዛ ነዋሪዎችን ለመደገፍ በየቀኑ 100 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መግባት አለባቸው ብለዋል።

የጥቅምት አስሩ የዕርዳታ ጭነት በቂ አይደለም

ሆኖም የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF)፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP)፣ የተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA)፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጋራ ባወጡት መግለጫ አሁን የተላከው ዕርዳታ ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ እንዳልሆነ አስጠንቅቀዋል። መግለጫው መስከረም 26 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ላይ አሰቃቂ ጥቃት ባደረሰው ቀውስ በርካታ ሰዎች እንደሞቱ እና ወደ 200 የሚገመቱ እስራኤላውያንን አግተው አሁንም ድረስ እንዳልተለቀቁ ይታወቃል።

በአስደንጋጭ ሁኔታ ብዙ ህፃናት እየሞቱ ነው

ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሆኑና “ህፃናት ጥበቃ፣ ምግብ፣ ውሃ እና የጤና አጠባበቅ መብታቸውን ተነፍገው በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየሞቱ ነው” ይላል መግለጫው። ለጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍሉት ልጆች ናቸው። እስራኤል በጋዛ ላይ ባደረሰችው የአጸፋ የአየር ጥቃት እስካሁን ከተገደሉት ከ4,500 በላይ ሰዎች አንድ ሶስተኛው የሚሆኑት ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ናቸው። ከነፍሰ ጡር እናቶች እና አዛውንቶች ጋር በመሆን ለሰብአዊ ቀውስ በጣም ከተጋለጡት መካከልም እንደሆኑ እሙን ነው።

እያንዳንዱ ልጅ ዬትም ዬት ሰላም ይገባዋል

ጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች ጀነሬተሮቻቸው የነዳጅ አቅርቦቶች እያገኙ ስላልሆነ ያለጊዜ ተወልደው ኢንኩቤተር ውስጥ ያሉ ሕፃናትን የመሞት አደጋ ስጋት ውስጥ እየከተታቸው ሲሆን፥ በጋዛ ቢያንስ 50,000 ነፍሰ ጡር ሴቶች አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን ማግኘት እንዳልቻሉም ተነግሯል። ከነዚህም ውስጥ በሚቀጥለው ወር 5,500 የሚሆኑት እናቶች ይወልዳሉ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ካትሪን ራስል “እያንዳንዱ ልጅ ዬትም ይሁን ዬት በሁሉም ቦታ ሰላም ይገባዋል” ሲሉ ካስጠነቀቁ በኋላ “የሰብአዊ አቅርቦቶችን በተከታታይ ማቅረብ ካልቻልን ለሕይወት አስጊ የሆነ የበሽታ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ስጋት ላይ ነን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሌሎች የነፍስ አድን አቅርቦቶችን ጨምሮ ዩኒሴፍ እስካሁን 50,000 ሊትር ነዳጅ እና የውሃ አቅርቦቶችን በማቅረብ 800,000 ሰዎች አነስተኛ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እንዲያገኙ አድርጓል። የዩኒሴፍ ንብረት የሆነው እና አሁንም በሥራ ላይ የሚገኘው ጨዋማ ውሃን የሚያጣራው የውሃ ማምረቻ ፋብሪካ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ብቸኛው ነው።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ ወላጆች የልጆቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እንዲረዳቸው በጋዛ ላሉ 1,000 ለሚሆኑ ቤተሰቦች የአደጋ ጊዜ የገንዘብ ዝውውር በማድረግ እግዛ እያደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
 

24 October 2023, 15:08