ፈልግ

በዱባይ የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በዱባይ የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ 

“ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ “COP28”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአንድ ሳምንት በፊት “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” የሚል አዲስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” የተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ በቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ እና በመጪው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ “COP28” መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት አስተያየቱን አጋርቶናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ከስምንት ዓመት በፊት ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ የሚለውን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ይፋ ያደረግሁበት ምክንያት፥ ስቃይ ውስጥ ለምትገኝ የጋራ ምድራችን ያለኝን ልባዊ አሳቢነት ለወንድሞቼ እና እህቶቼ ለማካፈል በመፈለጌ ነው። ሆኖም ጊዜ በሄደ ቁጥር የምንኖርበት ዓለም እየፈራረሰ ወደ መሰባበር ደረጃ እየተቃረበ ሳለ የእኛ ምላሽ በቂ ሆኖ አለመገኘቱን ተረድቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ተጽዕኖ በበርካታ ሰዎች እና ቤተሰቦች ሕይወት ላይ ጉዳት እያስከተለ እንዲሄድ ማድረጉ የማይታበል ጉዳይ ነው። በጤና አጠባበቅ፣ በሥራ ዕድሎች፣ በተፈጥሮ ሃብቶች ተደራሽነት፣ በመኖሪያ ቤት አገልግሎት፣ በግዳጅ ስደት ወዘተ ላይ ተጽዕኖ ማድረጉ ይገባናል።” ብለዋል። (2) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” በተሰኘው አዲሱ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ውስጥ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ለአየር ንብረት ቀውስ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ለማሳሰብ ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ በግልጽ እናገኛለን።

በዱባይ ከኅዳር 20 እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ. ም. ድረስ ለሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) አጭር ቢሆንም ነገር ግን ብዙ ጠንካራ አንቀጾች ያሉበትን ጳጳሳዊ ሠነድ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ይፋ አድርገዋል። ቅድስት መንበርን ጨምሮ 198 ሀገራት ጉባኤውን ይቀላቀላሉ። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ መስከረም 30/2016 ዓ. ም. የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ፕሬዚደንት ክቡር ዶ/ር ሱልጣን አህመድ አል ጃብርን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው ይታወሳል።

"የሰው ልጅ ጥቃቅን ፍላጎቶቹን አልፎ በትልቁ ለማሰብ ባለው አቅም ላይ እርግጠኞች ከሆንን፥ በቀጣዩ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ (COP28) ጉባኤ ላይ ቁርጠኝነት ያለው ውጤታማ የሆነ ወሳኝ የኃይል ሽግግር ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ጉባኤ፥ ከ1992 ጀምሮ የተደረገው ጥረት ውጤታማ አለመሆኑን በማመልከት የአቅጣጫ ለውጥን ሊያመጣ ይችላል። አለበለዚያ ትልቅ ተስፋ አስቆራጭ እና እስካሁን የተገኘውን ማንኛውንም መልካም ነገር አደጋ ላይ ይጥላል"። (54)

ይህን ቁጭት ማስወገድ የሁሉም ሰው ሃላፊነት ነው፡ ይህም በ “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ተዋናዮችን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሂደት ነው። መስተጋብርያቸው በአካባቢ ጉዳይ ወይም ድንገተኛ ፍላጎቶች ሥነ-ምግባራዊ የበላይነት እንዲሰፍን ያደርጋል በሚል እምነት፥ (39) በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ውስጥ ለተወገዘው የህሊና እና የኃላፊነት ውድቀት ምላሽ ይሰጣል። (169) የመጀመሪያው ተዋናይ የሳይንስ ማኅበረሰብ ሲሆን፥ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ለማጉላት ቁርጠኛ የሆነው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በመጀመሪያ ምዕራፉ ያሳስበናል።

ይህ “ትንቢታዊ” ማሳሰቢያ ይፋ ከሆነበት ከስምንት ዓመታት በኋላ የወጣው “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” የሚለው አዲስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ፥ ከዚህ በኋላ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ምክንያቱ የሰው ልጅ መሆኑን መጠራጠር አይቻልም” (11) በማለት ያስረዳል። በሚያሳዝን ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አሁን ማቆም አንችልም”። ከዚህ የበለጡ አሳዛኝ ጉዳቶችን ለመከላከል ጊዜም የለንም” (16) ይህን አሳሳቢ ምልከታ ስንጋፈጥ ተረጋግቶ መቀመት ወይም ግዴለሾች መሆን አንችልም። ነገር ግን የዕድገቶችን አስደናቂ ነገሮች ለመገመት የሚያስችለን ሰፋ ያለ አመለካከት ሊኖረን ያስፈልጋል። ምናልባት ከመቶ ዓመት በፊት ሊታሰቡ የማይችሉ ሌሎች ተፅዕኖዎችን ትኩረት ሰጥተን እንከታተላለን። (18)

ሁለተኛው ተዋናይ የሥራ ፈጠራ ዓለም ነው። የሥራ ፈጠራ ዓለም ከሳይንስ ማኅበረሰብ ለሚነሳው አስቸኳይ ጥያቄ በንቃት ምላሽ መስጠት እና ፈጣን የሽግግር ጥበብን በማስተዋወቅ፥ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብ ይገባል” የሚለው ተዋናዩ የሚጫወተው ከፍተኛ ሚና ነው። እንደ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ፥ “የንግዱ ዓለም ሃብትን ለመሰብሰብ እና ዓለማችንን ለማሻሻል የታሰበ ትልቁ እና የተከበረ ሥራ ነው። በተለይም የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ለጋራ ጥቅም አገልግሎቱ አስፈላጊ አካል አድርገን የምንመለከተው ከሆነ ፍሬያማ የብልጽግና ምንጭ ሊሆን ይችላል።” (129) ከዚህ አንፃር “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” የሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ፥ “በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት የቅሪተ አካል ነዳጆችን አጠቃቀም በመቀነስ እና ንፁህ የሃይል ምንጮችን በማዳበር የሥራ ዕድል ቁጥ እንደሚቀንስ በተደጋጋሚ ይሰማል። እየተከሰተ ያለው በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን እያጡ ነው። የባሕር ከፍታ መጨመር፣ ድርቅ እና ሌሎች በምድራችን ላይ የሚታዩ ክስተቶች ብዙ ሰዎችን ለሞት ተዳርገዋል። በአንፃሩ ወደ ታዳሽ የኃይል ዓይነቶች የሚደረገው ሽግግር በአግባቡ የተደራጀ፣ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመላመድ የሚደረገው ጥረት በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይችላል። ይህም ፖለቲከኞች እና የንግዱ ዓለም መሪዎች አሁን ስለ ራሳቸው እንዲጨነቁ ያስገድዳቸዋል።” (10)

ይህ ሦስተኛ ተዋናይ በሆኑ ወጣቶች እና አዲስ ትውልዶች ላይ ብቻ አዎንታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። “ከእኛ የሚፈለገው ይህን ዓለም ካለፍን በኋላ ለምንተወው ውርስ የተወሰነ ኃላፊነት እንዲኖረን እንጂ ሌላ አይደለም” (18) የሚለው “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” አዲስ እና ግልጽ ማሳሰቢያ ወደ እነርሱ እንደዞረ ማስተዋል ቀላል ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ ነሐሴ 3/2023 በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረጉት ንግግር እናስታውሳለን። “የሰውን ልጅ ማዕከል በማድረግ ለሕይወት ክብርን የሚሰጥ አዲስ ጥበብን ለማስተዋወቅ መሥራት አለባችሁ። ይህን የምነግራቸሁ የዕድሜ ባለ ጸጋ የሆንኩ እኔ ነኝና! እንዲሁም ትውልዳችሁ የአስተማሪ ትውልድ እንደሚሆን አልሙ! ያውም የሰው ልጆች አስተማሪ፤ የርህራሄ አስተማሪ፤ ለምድራችን እና ለነዋሪዎቿ አዳዲስ ዕድሎችን የሚያስተምር፤ የተስፋ አስተማሪ። ዛሬ ለከባድ የሥነ-ምህዳር ጉዳት የተጋረጠውን የምድራችንን ሕይወት ከጉዳት የሚከላከል አስተማሪ" እዚህ ላይ የትምህርት እና የሥልጠና አስፈላጊነትን ማስታወስ ያስፈልጋል።

አራተኛው ተዋናይ ሲቪሉ ማኅበረሰብ ነው። የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መልዕክት በማስተጋባት፥ በሲቪል ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ብዙ ቡድኖች እና ድርጅቶች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጉድለቶች ለማካካስ ይረዳሉ። በተወሳሰቡ ሁኔታዎች መካከል ቅንጅት አለመኖሩ፣ ለመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ትኩረት አለመስጠቱ” (175)፣ “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” የሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ “ግሎባላይዜሽን” ድንገተኛ የባሕል ልውውጥን፣ የበለጠ የጋራ ዕውቀትን እና የሕዝቦች ውህደት ሂደቶችን በአማካይ ደረጃ ይደግፋል። ይህም የጋራ ዓላማ ያላቸውን መንግሥታት የሚያነሳሳ እንጂ በስልጣን ልሂቃን ብቻ የሚወሰን አይደለም። ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የማኅበረሰብ አንቂዎች እርስ በርስ በመደጋገፍ በመላው ዓለም ከታች የሚነሱ ጥያቄዎች በመያዝ በባለ ስልጣን ላይ ጫናን ሊፈጥሩ ይችላሉ። የአየር ንብረት ቀውስን በተመለከተ ይህ እንደከሰት ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል” (38)

አምስተኛው ተዋናይ መንግሥታትን ይመለከታል። የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ (COP28) በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አስተናጋጅነት ይመራል። ከፍተኛ የቅሪተ አካል ነዳጆችን ወደ ውጭ የምትልክ እና ለ20 ዓመታት ያህል የኃይል ሽግግር እያደረገች የምትገኝ አገር ናት። እንደ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ፕሬዝዳንትነት፣ አራት ቁልፍ ነጥቦች ያሉትን የድርጊት አጀንዳን አዘጋጅታለች። እነርሱም፥ ፈጣን እና ፍትሃዊ የሃይል ሽግግርን መከታተል፣ የአየር ንብረት ፋይናንስን ማስተካከል፣ በሰዎች፣ በተፈጥሮ፣ በብዝሃ ሕይወት እና መተዳደሪያ ላይ ማተኮር እና ሌሎች ነገሮችን በሙሉ ማካተት የሚሉት ናቸው። “አዳዲስ ኃይሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ተዛማች እየሆኑ መጥተዋል እና ተጨባጭ ችግሮችን ለመፍታት ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ...። ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆንም የችግሮች መልሶች ከየትኛውም አገር ሊመጡ የሚችሉ መሆናቸው፥ ወገንተኝነትን እንደ አንድ የማይቀር ሂደት አድሮ ማቅረብ ያስቀራል።” (40) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) አወንታዊ ውጤቶችን በማምጣት ሁሉም ሰው ተስፋ እንዲኖረው ያበረታታሉ።

እንደውም “የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው ከፊት ለፊቱ ለጋራ ጥቅም እና በልጆቻችን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ በማተኮር ለሽግግሩ እውነተኛ መነሳሳትን ለመስጠት ጠቃሚ ዕድል እንዳለው፣ ውጤታማ መፍትሄዎች ከግለሰቦች ጥረት ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወሰዱ ዋና ዋና የፖለቲካ ውሳኔዎች ሊሆኑ ይችላሉ።” (69) "ሁሉም ነገር እርስ በራሱ የተገናኘ ስለሆነ ማንም ሰው ሊደርስ ከሚችል አደጋ ብቻውን ሊተርፍ እንደማይችል” (19) እና “ከባሕል ለውጥ በቀር ሌላ ዘላቂ ለውጥ እንደሌለ፣ ለሰው ልጅ ዛሬ እና ነገ ሁሉንም ዓይነት ተሳትፎ የሚጠይቅ ውስብስብ እና አስፈላጊ ሂደት መኖሩን በመገንዘብ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ለውጦችን፣ የአኗኗር ዘይቤዎችን እና እምነትን ካላሳደጉ በቀረ የግል እና የባሕል ለውጦችን ማምጣት እንደማይቻል” (70) እና "የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ቦታ ለመውሰድ ሲሉ የራሳቸው ጠላቶች እንደሚሆኑ" (73) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ውዳሴ ለእግዚአሔር ይሁን” በሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ላይ ገልጸውታል።

 

 

12 October 2023, 16:43