ፈልግ

ፍልስጤማውያን ወደ ደቡብ ጋዛ እየሸሹ ፍልስጤማውያን ወደ ደቡብ ጋዛ እየሸሹ  (ANSA)

የተ.መ.ድ. የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየጠየቀ ባለበት ወቅት ፍልስጤማውያን ከጋዛ እየሸሹ ነው ተባለ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ያቀረበችው ጥሪ እጅግ አደገኛ መሆኑን እና የሰብአዊ እርዳታን እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ የሚኖሩ ሲቪሎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ለመውጫ በተሰየሙ መንገዶች ወደ ደቡብ እንዲያቀኑ ለተጨማሪ ጥቂት ሰዓታት እንደሚፈቅድ ተናግሯል።
ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር ሊሰነዘር ይችላል ተብሎ ለሚጠበቀው ጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ባለፈው አርብ ዕለት ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተነግሯቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ጥሪ

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዝግ በተደረገው ስብሰባ በጋዛ ለሚደረገው የሰብአዊ ዕርዳታ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪዎች ሊደረጉ የሚችሉባቸውን መንገዶች ሲወያይ ቆይቷል። ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደተናገሩት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በጦርነት ቀጠና ውስጥ ማንቀሳቀስ እጅግ አደገኛ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የዓለም ጤና ድርጅት ለአስቸኳይ የጤና ፍላጎቶች የሚረዱ የህክምና ቁሳቁሶችን የያዘ አውሮፕላን ከጋዛ በ28 ማይል ርቀት ላይ በምትገኘው በግብጿ አሪሽ ከተማ ማረፉን ገልጿል። ድርጅቱ አክሎም የሰብአዊ አገልግሎት መስጫ የድንበር ማቋረጫ መንገዶች እንደተከፈቱ አቅርቦቶቹን ወደ ጋዛ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነ አሳውቋል።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ባካሄደችው የቦምብ ጥቃት ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን አሁናዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የሃማስ ተዋጊዎች በሰላማዊ ሰዎች እና ወታደሮች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የእስራኤልን ድንበር ጥሰው በገቡበት ወቅት ከ1,300 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል።
 

16 October 2023, 14:12