ፈልግ

2023.03.14 traffico esseri umani, tratta

ተቀያያሪ እና ተለዋዋጭ የሆኑት የሰው አዘዋዋሪዎች ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር በመላመድ እየሰሩ ነው ተባለ

የባርነት፣ ብዝበዛ እና ጭቆና ምርምር ማዕከል የሆነው የለንደኑ ባኪታ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ካሮል መርፊ፥ ዘመቻ አድራጊዎች “እንደ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተቀያያሪ እና ተለዋዋጭ መሆን አለባቸው” ይላሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. በ1869 አካባቢ ሱዳን ውስጥ የተወለደችው ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ በለጋ ዕድሜዋ ለባርነት ተሽጣ ወደ ጣሊያን ከተወሰደች በኋላ በመጨረሻ በካኖሲያን እህቶች እርዳታ ነፃነቷን አገኘች። ቀሪውን ዘመኗን መነኩሴ ሆና ካገለገለች በኋላ በ2000 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቅድስና ማዕረግ ተሰጥቷታል። ዛሬ ላይ የለንደኑ ባኪታ ማእከልም በስሟ እየተጠራ ይገኛል።

በእንግሊዟ የትዊከንሃም ከተማ በሚገኘው የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተው ማዕከሉ በባርነት፣ ብዝበዛ እና በደል ላይ የጥናት እና ምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የድርጅቱ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ካሮል መርፊ በቅርቡ በሮም ተገኝተው ስለ ሥራቸው እና አሁን ላይ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ስላሉበት ሁኔታ ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ አርገዋል።

ምርምር እና ልምምድ

ዶ/ር መርፊ እንዳብራሩት የባኪታ ማዕከል እ.አ.አ. በ2015 የተቋቋመ ሲሆን፥ ዓላማውም “በፖሊሲ እና በተግባር ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ” ምርምር ለማድረግ ነበር። ይህ ማዕከል ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እስከ የስደተኞች አገልግሎቶች ባሉ ዘርፎች በ“በተግባር ልምምዶች” እና በአካዳሚክ ዕውቀት ልምድ ባላቸው ሠራተኞች የተሞላ እንደሆነም ዶክተር መርፊ ተናግረዋል። በተጨማሪም ማዕከሉ ዘመናዊ ባርነትን የመከላከል ሥራ ለሚሰሩ ሰዎች እንዲሁም ከአደጋው በሕይወት ለተረፉ ሰዎች የትምህርት አገልግሎት እንደሚሰጥም ተመላክቷል።

የችግሩ መጠን

ዶ/ር መርፊ አሁን ባለንበት ዘመን ላይ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር ምን ያህል እንደሆነ ተጠይቀው “በአብዛኛዎቹ የዓለም ሀገራት የህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑ በርካታ ሰዎች ስላሉ በእውነት መልስ መስጠት በጣም ከባድ ነው” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። እነዚህ ሰለባዎች ሁለቱን የአገሬው ተወላጆችን እና ከሌላ ሃገር የመጡትን ሰዎች ጭምር ያካትታል። የባሂታ ማእከል በጣም የቅርብ ጊዜ የምርምር ፕሮጀክቶች እንደሚያሳዩት የብሪታንያ ዜጎችም የችግሩ ሰለባ ሆነው በእንግሊዝ ውስጥ እንደሚገኙ ያመላክታል።

በሰው ዘንድ ከሚታመነው አስተሳሰብ በተቃራኒ፥ ዶ/ር መርፊ እንዳሉት የብሪታንያ ዜጎች በእንግሊዝ ውስጥ በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ካሉት ሰለባዎች አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ። ይሁን እንጂ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው የውጭ ዜጎችም እንዳሉ ገልጸዋል።

“ከአደጋው ለተረፉት ሰለባዎች የትምህርት ፕሮግራሞችን አዘጋጅተን እናስተምራቸዋለን” ሲሉ ዶ/ር መርፊ ከትናገሩ በኋላ አክለውም “ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአንጎላ፣ ጓያና፣ አልባኒያ፣ ቬትናም፣ ፊሊፒንስ፣ ናይጄሪያ፣ ቻይና የመጡ ሰዎች ነበሩን። እነዚህን ሁሉ ደግፈናቸዋል” ብለዋል።

"ማዕከሉ ውስጥ አብረውን ከሚሰሩት መካከል አንዳንዶቹ በአሳ ማጥመጃ ጀልባዎች ላይ በግዳጅ ይሰሩ የነበሩ እና ከጀልባው ላይ ወርደው ዬትም እንዳይሄዱ ተከልክለው የነበሩ ሰዎች ናቸው። ሌሎች ደግሞ ቪዛዎቻቸው አሰሪዎቻቸው ጋር ስለሚቀመጥ እና ሪፖርት ማድረግ ስለማይችሉ በሥራቸው ላይ የተለያዩ እንግልቶች ይደርስባቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።

አጸፋዊ እርምጃዎች

“እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ‘በእርግጥም ውስብስብ’ ነው፣ ምክንያቱም ይህንን የሚያደርጉት የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ናቸው፥ ነገር ግን በጣም የተበታተኑ እና ያልተደራጁ ቡድኖችም በቀላሉ ተጋላጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን በማጥመድ ህገወጥ የሰዎችን ዝውውርን ይፈጽማሉ” በማለት ተናግረዋል።

ዶ/ር መርፊ ስለ አዘዋዋሪዎቹ አሰራር ሲናገሩ “እንደ አለመታደል ሆኖ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከሁኔታዎች ጋር በመላመድ ረገድ በጣም ጥሩ ናቸው። አሰራራቸውን በየጊዜው ይቀያይራሉ። ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት እነሱ በሚችሉት መጠን ተለዋዋጭ እና ተቀያያሪ መሆን አለብን ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

በሮም የተካሄደው የፓናል ውይይት

ዶ/ር መርፊ በካቶሊክ ገዳማዊያት እህቶች የሚተዳደረው የፀረ-ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተቋም በሆነው በታሊታ ኩም እና በቅድስት መንበር የእንግሊዝ ኤምባሲ በጋራ ባዘጋጁት በትምህርት እና በዘመናዊ ባርነት ላይ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት መድረክ ላይ ንግግር ለማድረግ ሮም ተገኝተው ነበር። በዝግጅቱ ላይ ሌሎች ተናጋሪዎችም የነበሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሲስተር አንጄላ ኔሚላኪ እና ሲስተር አዲና ባላን ከታሊታ ኩም እንዲሁም በቅድስት መንበር የብሪታኒያ ኤምባሲ ምክትል ሀላፊ የሆኑት ዶክተር አናቤል ኢንጌ ይገኙበታል።

ሲስተር ኔሚላኪ እና ሲስተር ባላን በአፍሪካ እና በአውሮፓ ውስጥ ባሉ ዘመናዊ ባርነትን ለመዋጋት እየሰሩ ስላሉት ሥራ አንስተው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ ዶ/ር ኢንጌ በበኩላቸው እንደ ታሊታ ኩም ያሉ በሃይማኖት ተቋማት ላይ ተመስርተው የተቋቋሙ ማዕከሎችን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማሸነፍ ‘ወሳኝ’ ሚና እንዳላቸው በንግግራቸው ውስጥ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።
 

23 October 2023, 15:03