ፈልግ

የማህሳ አሚኒ ምስል የማህሳ አሚኒ ምስል  (AFP or licensors)

የአውሮፓ ፓርላማ የሳካሮቭ ሽልማትን ለኢራናዊቷ ማህሳ አሚኒ ሰጠ

የአውሮፓ ፓርላማ ባለፈው ዓመት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ለሞተችዋ ኢራናዊት ማህሳ አሚኒ እና በኢራን ለሚገኘው “ሴት፣ ህይወት፣ ነፃነት” ንቅናቄ ዓመታዊ የሳካሮቭ የሃሳብ ነፃነት ሽልማትን ሸልሟል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአውሮፓ ፓርላማ ባለፈው ዓመት በኢራን ፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ለሞተችው ማህሳ አሚኒ እና ኢራን ውስጥ ለሚንቀሳቀሱት የሴቶች ንቅናቄ ዓመታዊ የሳካሮቭ ሽልማትን ሰጠ። ለአስተሳሰብ ነፃነት የሚሰጠው የሳካሮቭ ሽልማት በአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብት ላይ ለሚሰሩ ሰዎች የሚከፈለው ከፍተኛው የምስጋና መግለጫ ሽልማት ነው።

የሳካሮቭ ሽልማት

‘የሃሳብ ነፃነት የሳካሮቭ ሽልማት’ የአስተሳሰብ ነፃነትን እንዲሰፍን የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች እውቅና ይሰጣል። ሽልማቱ በየዓመቱ በአውሮፓ ፓርላማ የሚሰጥ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ1988 ዓ.ም የተቋቋመው ይህ ሽልማት ለሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች የሚሟገቱ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ለማክበር ተብሎ የተመሰረተ እና የሶቪየት ህብረት የፊዚክስ ሊቅ እና የፖለቲካ ተቃዋሚ የሆነው አንድሬ ሳካሮቭን ለመዘከር የተሰየመ ሲሆን፥ ለተሸላሚዎችም 50, 000 ዩሮን ይሰጣል።

የአውሮፓ ህብረት በሽልማቱ እና በተዛማጅ ግንኙነቶቹ በኩል ጉዳያቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት መደገፍ የሚገባቸውን ተሸላሚዎችን ይረዳል። ሽልማቱም ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ. በ1988 ለኔልሰን ማንዴላ እና ለአናቶሊ ማርቼንኮ ተሰጥቷል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ፕሬዝዳንት የህኑት ሮቤርታ ሜሶላ በሰጡት መግለጫ “መስከረም 5 ጂና ማህሳ አሚኒ ኢራን ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ከተገደለች አንድ ዓመት አስቆጥሯል፥ የአውሮፓ ፓርላማ ኢራን ውስጥ ለእኩልነት፣ ለማንነት ክብር እና ለነፃነት ትግል ከሚያደርጉ ደፋር እና ቆራጥ ሰዎች ጋር በኩራት ይቆማል” ካሉ በኋላ “እነሱን እንደ ተሸላሚ በመምረጥ፣ ይህ ምክር ቤት ትግላቸውን እንደሚያስታውስ እና ለነፃነት ከፍተኛውን ዋጋ የከፈሉትን ሁሉ እያከበረ እንደሚቀጥል” ተናግረዋል።

በኢራን የሴቶች እንቅስቃሴ ተምሳሌቷ ማህሳ አሚኒ

በኢራን ምዕራባዊ ኩርዲስታን ግዛት የተወለደችው የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ የኢስላሚክ ሪፐብሊክ የግዴታ አለባበስ ህግን ተላልፋለች ተብሎ በፖሊስ ተይዛ ከታሰረች በኋላ ህይወቷ አልፏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የአሚኒ ቤተሰቦች በጭንቅላቷ እና እግሮቿ ላይ በደረሰው ድብደባ ምክንያት መገደሏን ሲገልጹ፥ ባለሥልጣናቱ ግን በነበሩት የሕክምና ችግሮች ህይወቷ አልፏል ብለዋል።

የማህሳ አሚኒ ሞት ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ በመቀስቀስ እና መጨረሻም በኢራን ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዥንብር በመፍጠር፥ እ.አ.አ. በ1979 ከተደረገው የእስልምና አብዮት በኋላ የተከሰተ ተቃውሞ በመሆን ተመዝግቧል።
“ሴት፣ ህይወት፣ ነፃነት” በሚል ባነር ስር የኢራን ዜጎች ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፍኑ እና የማይመጥን ልብስ እንዲለብሱ የሚደነግገውን ህግ በመቃወም ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ። የኢራን የጸጥታ ሃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱትን ጥብቅ ቁጥጥር በመቀጠል የአሚኒን አባት የማህሳ የሙት ዓመት ላይ ለአጭር ጊዜ ማሰራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
 

20 October 2023, 15:14