ፈልግ

 እስራኤል ካሃን ዩንስ ላይ  ጥቃት ካደረሰች በኋላ ፍልስጤማውያን ከህንጻ ፍርስራሽ ውስጥ አስከሬን እያወጡ እስራኤል ካሃን ዩንስ ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ ፍልስጤማውያን ከህንጻ ፍርስራሽ ውስጥ አስከሬን እያወጡ  (AFP or licensors)

ለጋዛ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንደሚናገሩት እስራኤል የቦምብ ድብደባዋን በቀጠለችበት በአሁኑ ሰዓት የጋዛ ሰርጥ አከባቢ ወደ ውድመት እያመራ እንደሆነ እየገለፁ ይገኛሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች አስቸኳይ እርዳታ ወደ ጋዛ ማድረስ እንዲፈቀድ ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። ይሄንንም ጥሪ ያደረጉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች በራፋ ማቋረጫ በኩል ለማለፍ እየተጠባበቁ ባለበት ጊዜ እንደሆነ ተመላክቷል። ከሳምንት በላይ በሆነው አጠቃላይ እገዳ ምክንያት የነዳጅ፣ የምግብ እና የውሃ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

እነዚህ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንደሚገልፁት ‘ሆስፒታሎች የነበራቸውን ጥቂት ነዳጅ ጨርሰዋል፥ የጋዛ ሰርጥ ጨርሶውኑ 'ወደ ጥፋት ጎዳና እያመራ ነው’ ብለዋል ። የምግብ አቅርቦቶች ዝቅተኛ በሆኑበት የሰሜን ጋዛ ሆስፒታሎች ውስጥ ከ 2,000 በላይ ታካሚዎች እንዳሉ ይታሰባል። አንዳንዶቹ በቅርብ የወለዱ እናቶች፣ የካንሰር ታማሚዎች ወይም የህይወት ድጋፍ መስጫ መሳሪያ ላይ ያሉ እና መንቀሳቀስ የማይችሉ ታማሚዎች ናቸው።

ይህ ሁሉ ሲሆን እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የቦምብ ድብደባ እንደቀጠለች ሲሆን፥ በአንድ ምሽት በደረሰ የአየር ጥቃት በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ 23 ሰዎችን ጨምሮ ከደርዘን በላይ የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እያለ ጋዛ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ማከሰኞ ምሽት የተፈጸመውን ጥቃት እንዳላደረሰች የገለጸችው እስራኤል ረቡዕ ጠዋት በተለያዩ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች። በሆስፒታሉ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፤ ሐማስ እስራኤልን፣ አስራኤል ደግሞ የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለውን ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ እያደረጉ ነው። የእስራኤል አየር ኃይል ዛሬ ጠዋት በተለያዩ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች ባሉ ወታደራዊ ያላቸውን ዒላማዎች የመታ መሆኑን ገልጾ፣ በዚህም የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን ሁለት አባላትን “መደምሰሷን” አሳውቃለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ለመወያየት ዛሬ ረቡዕ ረፋድ አምስት ሰዓት አካባቢ እስራኤል ገብተዋል። በእራኤል እና በጋዛ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሳምንት በኋላ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተጓዙት ፕሬዝዳንት ባይደን፣ ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊያቸውን ወደ አካባቢ ልከው ነበር። ግጭቱ እየተባባሰ እና የዓለም አገራትን ትኩረት መሳቡን ተከትሎ ባይደን እንደ አሜሪካ ፕሬዝዳንት አሁን ወደ ግጭት አካባቢ ያደረጉት ጉዞ ያልተለመደ ነው እየተባለ ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ግጭቶች ወደ ሚካሄዱባቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ማስታወቂያ እምብዛም ጉብኝት ማድረጋቸው የተለመደ አይደለም።
የጀርመኑ ቻንስለርም ወደ እስራኤል እንደሚያቀኑ እና ግጭቱ እንዳይባባስ ብሎም ለማስቆም እንዲቻል የማያቋርጥ ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

እንደሚታወቀው ግጭቱ የተቀሰቀሰው ከአስር ቀናት በፊት የሃማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ድንበር ዘልቀው ገብተው በወሰዱት አሰቃቂ ጥቃት 1,400 ሰዎችን በመግደላቸው እና ቢያንስ 190 ሰዎችን በተለይም ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ ሲቪሎች አግተው ወደ ጋዛ በመውሰዳቸው ምክንያት ነበር።
 

18 October 2023, 14:11