ፈልግ

በሉዊስተን የጅምላ ጥቃት በተፈፀመበት ቦታ የFBI መረጃ ምላሽ ቡድን አባላት እና የግዛቱ ፖሊስ አባላት ተሰብስበው። በሉዊስተን የጅምላ ጥቃት በተፈፀመበት ቦታ የFBI መረጃ ምላሽ ቡድን አባላት እና የግዛቱ ፖሊስ አባላት ተሰብስበው።  (2023 Getty Images)

የፖርትላንድ ሊቀጳጳስ በአሜሪካዋ ሉዊስተን ከተማ በደረሰው የጅምላ ተኩስ ጥቃት በጣም ማዘናቸውን ገለፁ

የፖርትላንድ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ሮበርት ዲሌይ የሰሜን ምስራቅ አሜሪካ ግዛት በሆነችው የሜይን ግዛት፥ በሉዊስተን ከተማ በጅምላ በጥይት ተደብድበው ለተገደሉ 18 ሰዎች ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ በጥቃቱ ለተጎዱ ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአሜሪካ ፖሊሶች ጥቅምት 14, 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በሜይን ግዛት በሉዊስተን ከተማ 18 ሰዎችን በጥይት ገድሎ ሌሎች 13 ሰዎችን አቁስሏል ተብሎ የተጠረጠረውን የ40 ዓመቱን ተጠባባቂ የጦር ኃይል አባልን እያደኑ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የሰለጠነ የጦር መሳሪያ አስተማሪ እና የአሜሪካ ተጠባባቂ የጦር ሃይል አባል የሆነዉ ሮበርት ካርድ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለበት በቅርብ ጊዜ ተዘግቦ ነበር።

ሮበርት ጥቃቱን በፈፀመበት ቀን በአካባቢዉ ወደሚገኝ ቦውሊንግ መጫወቻ አከባቢ በመሄድ ከዚያም በአቅራቢያው በሚገኝ ምግብ ቤት ውስጥ በመግባት በከፊል አውቶማቲክ መሳሪያው የጥይት ናዳ ሰላማዊ ሰዎች ላይ መተኮስ ጀመረ። ተጠርጣሪው አቶ ሮበርት ይሄንን ሁሉ ካደረገ በኋል ሳይያዝ አሁንም በሽሽት ላይ እንደሆነ ተነግሯል።

የፖርትላንዱ ሊቀጳጳስ ሮበርት ዲሌይ የጸሎት ጥሪ

የፖርትላንድ ሊቀጳጳስ የሆኑት ሮበርት ዲሌይ በጥቃቱ ለተጎዱት ንጹሃን ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የፖርትላንድ ጳጳስ አቡነ ሮበርት ዴሊ ለሊዊስተኑ እልቂት ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት ምላሽ “ከባድ ሀዘን እንደተሰማቸው” ገልፀዋል። አቡኑ ምእመናን “በዚህ አሰቃቂ ጥቃት ለተጎዱት ሁሉ” እንዲሁም የተጎዱትን ለሚንከባከቡ የሆስፒታል ሰራተኞች እና ቀሳውስት እንዲጸልዩ ጋብዘዋል።

ጳጳስ ዲሌይ “በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ተስፋ ማድረግ የማይቻል ቢመስልም አፍቃሪ የሆነው አምላክ እንደማይተወን በመተማመን ከመንፈሳዊ መሰረቶቻችን በመነሳት ተስፋን መሰነቅ እንችላለን” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል። “በተለያዩ መንገዶቻችን ወደ እርሱ ስንጸልይ፥ እርሱ ያበረታናል፣ በመጪው አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ወደፊት እንድንራመድ መንገዱን ያሳየናል” በማለትም አክለው ጽፈዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ አሜሪካ ቢያንስ 565 የጅምላ ተኩስ ጥቃት ተፈፅሞባታል ሲል የመሳሪያ ጥቃቶችን መዝግቦ የሚያስቀምጠው (Gun Violence Archive) ተቋም ገልጿል።

"ትርጉም አልባ የጠመንጃ ጥቃት"

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሃገሪቱ ባንዲራዎች በኋይት ሀውስ ውስጥ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ካዘዙ በኋላ በሀገሪቱ ውስጥ በቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጅምላ የመሳሪያ ጥቃቶች መበራከታቸውን ተከትሎ የጠመንጃ ቁጥጥር እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል ።

ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስም በበኩላቸው ከልብ ማዘናቸውን ገልፀው “ማህበረሰቡ ትርጉም በሌለው የጠመንጃ ጥቃት እየተሰቃየ ነው” ብለዋል። በጥቃቱ ላይ በሚደረገው ምርመራ የተፈጠረውን ሁኔታ በማጣራት አስተዳደሩ ለአካባቢው ባለስልጣናት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድም በሰጡት መግለጫ “የሚወዷቸውን በሞት ላጡ፣ ለተጎዱ እና ለመላው የሉዊስተን ማህበረሰብ ከልቤ አዝኛለሁ” በማለት ሃዘናቸውን ገልፀዋል።
 

27 October 2023, 15:01