ፈልግ

ፍልስጤማዊ ሴት በፍርስራሾች መካከል እያለቀሰች። ፍልስጤማዊ ሴት በፍርስራሾች መካከል እያለቀሰች።  (AFP or licensors)

በጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ የተፈጸመው ጥቃት ‘ኢሰብአዊ ድርጊት’ ነው ተባለ

በጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው እልቂት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያስደነገጠ ሲሆን፥ ጦርነቱ ከሚገመተው በላይ እየተካሄደ ሊታሰብ የማይችሉ ውጤቶችን ሊያመጣ ቢችልም፥ ሰብአዊ ጥፋት ሊያደርሱ የሚችሉ ተግባራት ግን መወገድ እንዳለባቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቅምት 6, 2016 ዓ.ም. ማክሰኞ ምሽት ላይ ጋዛ በሚገኘው አል-አህሊ አረቢ በሚባለው የአንግሊካን ሆስፒታልን ላይ በደረሰ ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው እልቂት ኢሰብአዊ ድርጊት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፥ ጥቃቱ ብዙ ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል። 

ይህንን ጥቃት እንዳላደረሰች የገለጸችው እስራኤል ረቡዕ ጠዋት በተለያዩ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች።ሐማስ እስራኤልን፣ አስራኤል ደግሞ የፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተባለውን ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ እያደረጉ ነው። የእስራኤል አየር ኃይል ረቡዕ ጠዋት በተለያዩ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች ባሉ ወታደራዊ ያላቸውን ዒላማዎች የመታ መሆኑን ገልጾ፣ በዚህም የፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድን ሁለት አባላትን “መደምሰሷን” አሳውቃለች።

ጥቃቱ ማንም ይፈፅም ማን በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፥ በቅርቡ በቫቲካን ሚዲያ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን መስከረም 26, 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት እና ሰላማዊ ሰዎች በሆኑት በሴቶች እና በህጻናት ላይ የተፈፀመውን እልቂት ለመግለጽ “ኢሰብአዊነት” የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል።

ካርዲናሉ እስራኤላውያን እራሳቸውን የመከላከል እና በሃማስ ታጣቂዎች የሚደርሰውን የሽብር ጥቃት የመዋጋት መብት እንዳላቸው ደጋግመው ከገለፁ በኋላ፥ በተጨማሪም “ህጋዊ ራስን የመከላከል እርምጃው የተመጣጠነ መስፈርትን ማክበር አለበት” በማለት አስታውሰው፥ በጋዛ ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን እንዲታደጉ ጠይቀዋል።
የጋዛ ባለስልጣናት ከሃማስ ጋር በመሆን እስራኤል ከሲቪሎች እንዲጸዳ በጠየቀችበት አካባቢ የሚገኘውን ሆስፒታል ያወደመችው እስራኤል እንደሆነች ቢናገሩም፥ የእስራኤል መከላከያ ሃይል ግን በበኩሉ የጅምላ ጭፍጨፋውን በኢስላሚክ ጂሃድ የተወነጨፈው ሚሳኤል አቅጣጫውን በመሳት በሆስፒታሉ ላይ እንደወደቀ በመግለፅ ክሱ ትክክል አለመሆኑን እና ሃላፊነቱንም እንደማይቀበል አሳውቋል።

የሦስተኛው የዓለም ጦርነት ጅማሮ ምልክት በሚመስሉ እና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ እየተከሰቱ ባሉት ጦርነቶች በማስታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በፍጥነት ወደ አንድነት መምጣት እንዳለብን ካሳሰቡ በኋላ፥ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕጎችን ሳይረሱ የጥላቻን ስሜት በማስወገድ ሽብርተኝነትን ማሸነፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ቀድሞውኑ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት እና የተለያዩ ችግሮች የነበሩበትን ይሄንን ሆስፒታል የማውደም ወንጀል ማን እንደፈፀመ ይፋ እንዲደረግ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰብአዊ ጥፋትን ለመከላከል ጣልቃ እንዲገባ እና ይሄንን አስከፊ ውጤት ያለው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም መማጸን አለብን ብለዋል።

የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ጄምስ ክሌቨርሊ በቅርቡ እንደተናገሩት “ዩናይትድ ኪንግደም በሆስፒታሉ ውስጥ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ እና ንጹሃን ዜጎችን ለመጠበቅ” ከአጋሮቿ ጋር ትሰራለች” ካሉ በኋላ “የሲቪላዊያን ህይወት ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል። ስለተፈጠረው ነገር እውነታውን የማወቅ ጥያቄ ጋር የሌሎችም ድምጾች ከእሳቸው ጋር ይተባበራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በእስራኤል ንጹሃን ማህበረሰብ ላይ የተፈፀመው የአሸባሪዎች ጭፍጨፋ እና ኢሰብአዊነት በተሞላበት ሁኔታ በጋዛ ንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላምና ፍትሃዊ የወደፊት ተስፋን እንድንዘነጋ ሊያደርገን እንደማይገባም ተመላክቷል።

ከላይ በተገለጸው ቃለ ምልልስ ላይ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እንደተናገሩት “ለእኔ በቅድስት ሀገር ላይ እየተደረገ ላለው ጦርነት ትልቁ የፍትህ መፍትሄ መስሎ የሚታየኝ፥ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን መካከል በሰላምና በጸጥታ አብረው እንዲኖሩ የሚያስችለው የሁለቱንም ሃገራት ፍላጎቶች ያማከለ የሁለቱ ሃገራት የጋራ መፍትሄ ነው” ካሉ በኋላ “ቅድስት መንበር ይህንን የሁለትዮሽ የጋራ ምክክር በሁሉም መልኩ እየደገፈች እንደምትገኝ” አስረድተዋል። በመጨረሻም በሃማስ የተያዙት ሁሉም ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የሰብአዊ ህግን ሙሉ በሙሉ እንዲያከብሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
 

19 October 2023, 13:04