ፈልግ

የዓለም የተቀናጀ ሕክምና ባለሙያዎች ምክር ቤት ስብሰባ የዓለም የተቀናጀ ሕክምና ባለሙያዎች ምክር ቤት ስብሰባ  

የዓለም የተቀናጀ ሕክምና ባለሙያዎች ምክር ቤት ስብሰባ ሰውን ያማከለ ነው ተባለ

ከ50 ሀገራት የተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች በሮም ለ2ኛው የዓለም አቀፍ የተቀናጀ የመድሃኒት እና ጤና ምክር ቤት ጉባኤ በመሰብሰብ የተሻሻሉ ህመምን የማዳን ጥበብ አማራጮች ልማዳዊውን የህክምና አገልግሎት እንዴት እንደሚያሟሉ ይወያያሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከሕመማቸው ይልቅ በግለሰቡ ላይ የሚያተኩር ሁሉን አቀፍ አቀራረብ እና የተቀናጀ የህክምና አሰጣጥ ዋና መርህ ነው። ይህ ጽንሰ-ሐሳብ ይፋ የሆነው በሮም በተካሄደው እና በአርቶይ ፋውንዴሽን የተቀናጀ የዕጢ ህክምናዎች ላይ ምርምር ባዘጋጀው በሁለተኛው የዓለም የተቀናጀ ሕክምና እና ጤና ስብሰባ ላይ በተካሄደው የአራት ቀናት ውይይቶች ከዓለም አቀፉ ባሕላዊ፣ ተጨማሪ፣ እና የተቀናጀ ሕክምና ምርምር (ISCMR) እና ከአውሮፓ ህብረት ለተቀናጀ ሕክምና ጋር በመተባበር ባዘጋጁት ስብሰባ ላይ ነው።
ስብሰባው የዕጢ ህክምናን ፣ ኮቪድ-19ን፣ ድህረ ተላላፊ በሽታዎችን፣ የአመጋገብን እና የአኗኗር ዘይቤዎችን እንዲሁም ጥበብን እንደ ህክምና መሳሪያ መጠቀምን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ወሳኝ ጭብጦችን ያጠቃልላል። በዋናነትም ፥ የተቀናጀ ሕክምና አሰጣጥ ሂደቱ ባህላዊ ሕክምናን የዘመናዊ ህክምና የእንክብካቤ አሰጣጥ መሠረት አድርጎ ያስቀምጣል። ነገር ግን በጥንታዊ ባህሎች ውስጥ በተመሠረቱ ባህላዊ ሕክምናዎች፣ ተጨማሪ ልምምዶች እና የሕክምና አማራጮች የሚያሟሉ መሆን እንዳለባቸውም ያሳስባል።
በሳይንሳዊ ማስረጃዎች የተደገፉ እነዚህ አካሄዶች የህይወት ጥራትን እና የታካሚዎችን የመትረፍ መጠን ይጨምራሉ። እንደ ዕጢ ሕክምናዎች ያሉ የሚያመጡትን የጎንዮሽ ጉዳቶች በመቀነስ ለታካሚዎች ስሜታዊ እና አእምሮአዊ ደህንነት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
ስለዚህ ኮንግረሱ በሙከራ እና በክሊኒካዊ መቼቶች የተካሄዱ እጅግ በጣም ጥሩ ጥናቶችን እና ምርምሮችን እንዲሁም በዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ ስርዓቶች ውስጥ የመዋሃድ እና አብሮ የመስራት ልምዶችን ያቀርባል ፤ ይህም ሁለንተናዊ የጤና አሰጣጥ መንገድን በመለየት የተለያዩ ባለሙያዎች የሚያደርጉትን የትብብር ጥረት አጉልቶ ያሳያል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሚና

ለወደፊት የተቀናጀ እና ተጨማሪ ህክምና ትኩረት ተሰጥቶ የተነሳው በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ኮንግረስ የመክፈቻ ንግግር ወቅት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ የመክፈቻውን የከሰዓት ንግግር ያደረጉ ሲሆን ፥ የዓለም ጤና ድርጅት ባህላዊ፣ ተጨማሪ እና የተቀናጀ ህክምና ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሱንግቾል ኪም በሂደቱ ላይ በንቃት ተሳትፈዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ባለፈው ነሃሴ በህንድ ሃገር የተካሄደውን “ጤና እና ደህንነት ለሁሉም” በሚል የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ያስገኛቸውን ውጤቶች አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል። ያ ጉባኤ የዓለም ጤና ድርጅት የ2025-2034 ስትራቴጂ በባህላዊ፣ አጋዥ እና ውህደታዊ መድሃኒቶች ላይ የሚያተኩሩትን መርሆች እና እሴቶችን ዘርዝሯል።
ለዘመናት ባህላዊ እና ተጨማሪ ማሟያ ህክምናዎች የግለሰቦችን እና ማህበረሰቦችን ጤና ለማሻሻል ዓለም አቀፍ ግብአት ሆኖ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ከ 100 በላይ አገሮች ለእነዚህ መድሃኒቶች ብሔራዊ ፖሊሲዎችን ያቋቋሙ ሲሆን ፥ በግምት 40 በመቶው የፋርማሲዩቲካል ምርቶች ከተፈጥሯዊ ግብአቶች የተገኙ ናቸው። በዚህም ዘርፍ ጂኖሚክስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ፈጠራን እና ልማትን ጨምሮ አዳዲስ ምርምሮችን በማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተመላክቷል። የዓለም ጤና ድርጅት ስትራቴጂ እነዚህን መድሃኒቶች በጤና ፖሊሲዎች እና መጠቀሚያዎች ጋር በማዋሃድ ውጤታማ እና የሰዎችን መብቶች የሚያከብሩ ዘላቂነት ያላቸውን ሃብቶችን፣ አከባቢዎችን ፥ ግብአቶችን ፣ የአከባቢው ማህበረሰብ መብቶችን ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የጤና እና ደህንነትን ገጽታ የሚቀርጹ መሆናቸውን በመገንዘብ የተወጠነ ዕቅድ ነው።

የዕጢ ህክምና፣ ኮቪድ እና የልጆች ህክምና ላይ ያተኮሩ መርሃግብሮች እና አውደ ጥናቶች

ስብሰባው 850 የተመዘገቡ ተሳታፊዎች እና 550 ረቂቅ ጽሑፎችን ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት በመቀበል ብዙ ሰው የሚገኝበት አስደናቂ የተሳትፎ ጊዜ እንደሚያሳልፍ ተነግሯል። በሮም በሚገኘው አንጀሊኩም ኮንግረስ ማዕከልም 24 አውደ ጥናቶችን እያስተናገደ ይገኛል።
አብዛኛው የስብሰባው መርሃ ግብር የሚሆነው ለዚህ ዘመን እና ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆኑትን የህክምና አሰጣጦችን ማለትም የዕጢ ህክምናዎች ፣ የባህላዊ ህክምናዎችን ከተሻሻሉ ህመምን የማዳን ጥበቦች ማለትም እንደ የተፈጥሮ እና የእጽዋት ምርቶች፣ የሰውነት ሙቀት ከልክ በላይ የመጨመር (ሃይፐርቴርሚያ)፣ በተፈጥሮያዊ የሰውነት አወቃቀር ዜዴ ማከም (ሆሚዮፓቲ)፣ የአመጋገብ፣ አኩፓንቸር እና የአዕምሮ-የሰውነት ሕክምናን ከመሳሰሉ አማራጮች ጋር በማጣመር የመዋሃድ ተስፋዎች የታዩበት ናቸው።
ዝግጅቱ የህክምና ምርመራ ልምምድ እና በቴራፒስቶች እንዲሁም በጤና እንክብካቤ ባለሙያዎች ስልጠና ላይ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል። በተጨማሪም የዓለምን ገፅታ የቀየረውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ፣ የሕፃናት ሕክምና እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ድህረ-ተላላፊ በሽታዎች በመሳሰሉ ወሳኝ ርዕሶች ላይ በጥልቀት ይወያያል። እንዲሁም ኮንግረሱ የጥበብ እና የመድሃኒት ትሥሥር እና ግንኙነቶችን ይዳስሳል። በመጨረሻም፣ ተፈጥሮን፣ አካባቢን እና በዓለማችን ላይ ያሉ ሕያዋን ፍጥረታትን በማክበር የሁሉም ሰው ጤናን ለማስጠበቅ የተመራማሪዎች፣ የሃኪሞች እና የቴራፒስቶችን የሃሳብ እና የልምድ ልውውጥን ለማመቻቸት እና ትስስር ለመፍጠር ያለውን ወሳኝ ፈተና ይመለከታል።
 

21 September 2023, 13:45