ፈልግ

በሞስኮ የሚገኘው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት በሞስኮ የሚገኘው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት  (AFP or licensors)

ሩሲያ ተጨማሪ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣልዋን አስታወቀች።

ሩሲያ ማክሰኞ ዕለት ሞስኮን ኢላማ ያደረጉ በዩክሬን ጦር የሚመሩ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተኩሳ መጣሏን ተናግራለች። ይህ መግለጫ የወጣው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት ለማጠናከር ከሰሜን ኮሪያ ጋር በመገናኘት ድጋፍ እንድታረግላት ትጠይቃለች ተብሎ በተዘገበበት ወቅት ነው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ማክሰኞ ዕለት የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር የአየር ሃይሉ የሞስኮን አካባቢ በሚያዋስኑት በካሉጋ እና በቴቨር ክልሎች ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል። በተጨማሪም ለዋና ከተማዋ ሞስኮ ቅርብ በሆነቿ ኢስታራ አውራጃም አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን መጣላቸውን አክለው ተናግረዋል።
ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ሞስኮ የሚገኙት ዋና ዋና አውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎታቸው ተቋርጦ የነበረው ከሰው አልባ አውሮፕላኖቹ ጥቃት ለመታደግ ተብሎ እንደሆነም ገልፀዋል። ቀደም ሲል የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የመከላከያ ኃይሉ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ላይ ያነጣጠሩት እና በዩክሬን ጦር የሚመሩትን ቢያንስ ሶስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተኩሶ መጣሉን አስታውቋል።
ሞስኮ በበኩሏ የሩስያ አየር ሃይል መከላከያ በ 2006 ዓ.ም. ሩሲያ ከዩክሬን በወሰደችው የክሬሚያ ባሕረ ገብ መሬት ላይ የዩክሬንን ትልቅ ሰው አልባ አውሮፕላን መታ መጣሏን አስታውቃ ነበር።
የሰሞኑ ውዝግብ የተጀመረው አሜሪካ የሰሜን ኮሪያውን መሪ የሆኑት ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ወር ውስጥ ወደ ሩሲያ በማቅናት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በመገናኘት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለምታካሂደው ጦርነት መሳሪያ ለክሬምሊን ለማቅረብ እንደሚመክሩ ከተናገረች በኋላ ነው።
ኪየቭ የተወሰነ ግዛት አስመልሳለች በሚል ክስ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ወረራዋን ለመቀጠል ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ትፈልጋለች። የኪየቭ መንግስት ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው በሩሲያ ኃይሎች ላይ ባደረጉት የመልሶ ማጥቃት ወታደሮቿ በምስራቃዊ ግንባር ላይ ‘ተጨማሪ ግዛቶችን መልሰው’ ወደ ደቡብ እየገሰገሱ እንደሆነ ነው ። ይሁን እንጂ የኪየቭ መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱን በማመን ፥ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የናቶ ህብረት አባል በሆነችዋ የሩማንያ ግዛት በዳኑቤ ወንዝ ማዶ በሚገኘው የዩክሬን ወደብ ላይ ባደረጉት አንድ ሌሊት በፈጀ የአየር ላይ የቦንብ ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግሯል።

አልፎ አልፎ የሚከሰት ጥቃት

የሮማኒያ መንግስት ግዛቱ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ጥቃት እንዳልደረሰበት አስተባብሏል።
ሆኖም ግን በቪድዮ የተቀረጸው ምስል እንደሚያሳየው ቁልፍ ቦታ በሆነው የዛፖሪዝዝሂያ የጦር ግንባር በሆነው በዩክሬን ግዛት ስር በምትገኘው የሮቦቲኔ መንደር አቅራቢያ የእንግሊዝ ስሪት የሆነው ‘ቻሌንጀር 2’ የተባለው ታንክ መውደሙን በዚያ አከባቢ መኪና እያሽከረከረ ሲያልፍ የነበረ ሰው የቀረጸው እና የታየው ምስል እንደ ማስረጃነት ይታያል። ለዩክሬን ከተሰጡት ታንኮች ውስጥ አንዱ በውጊያ ሲወድም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል። ጥቃቱ የሩሲያ ሃይሎች የምዕራባውያንን ወታደራዊ ሃርድዌር ማጥቃት እንደሚችሉ ለማስታወስም ጭምር ነበር።
ግጭቶች ቀጥለው ባሉበት በዚህ ወቅት ፥ ምንም እንኳን እነዚህ የጦር መሳሪያዎች በብዙ አገሮች የተከለከሉ ቢሆንም ፥ የክላስተር ቦምቦችን መጠቀም እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢነቱም በዛው ልክ እየጨመረ ነው።
‘የክላስተር ቦምብ ታጣቂዎች ጥምረት’ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ባለፈው ዓመት ሩሲያ እነዚህን የተከለከሉ የጦር መሳሪያዎች ተጠቅማ ከ900 በላይ ሰዎች በዩክሬን “በክላስተር ቦምብ ጥቃቶች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል” ብሏል።
ክላስተር ቦምቦች በአየር ላይ ከመፈንዳታቸው እና ወደ ሰፊ ቦታ ከመበተናቸው በፊት ከአውሮፕላኖች ላይ ሊወነጨፉ ወይም እንደ መድፍ ሊተኮሱ ይችላሉ። እንዲሁም ብዙዎቹ በኢላማ ቦታቸው ላይ መፈንዳት ባለመቻላቸው እና ለረጅም ዓመታት ሳይፈነዱ ሊቁዩ የሚችሉ ፈንጂዎች ሆነው በመሰራታቸው ዘላቂ ስጋትን ይፈጥራሉ።
ይህ ጥምረት ታድያ አሁን ዩክሬን ከአሜሪካ የመጣውን አወዛጋቢ የጦር መሳሪያ ተከትሎም የክላስተር ቦምቦችን በብዛት ልትጠቀም እንደምትችል ያለውን ስጋት ገልጿል።
 

07 September 2023, 12:25