ፈልግ

በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሻራ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሻራ  (AFP or licensors)

የኔቶ ዋና ሃላፊ በዩክሬን የረጅም ጊዜ ጦርነት ሊኖር እንደሚችል ዓለምም ለዚህ እንዲዘጋጅ አስጠነቀቁ

የኔቶ ወታደራዊ ጥምረት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ጄንስ ስቶልተንበርግ የዩክሬን ጦርነት ፈጣን ማብቂያ እንደማይኖረው የዓለምን ማህበረሰብ አስጠንቅቀዋል። ይህ የሳቸው አስተያየት የመጣው ኪየቭ በሩሲያ ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ መጀመርዋን ተከትሎ ነው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኔቶ ዋና ፀሃፊ የሆኑት ጄንስ ስቶልተንበርግ እስካሁን በሰጡት ተጨባጭ አስተያየቶች አብዛኛው ጦርነቶች መጀመሪያ ሲጀምሩ ቶሎ ያልቃሉ ተብሎ እንደሚታሰበው ሳይሆን ከሚገመተው በላይ እንደሚቆዩ ጋዜጠኞችን አስታውሰዋል። በመሆኑም እንደእርሳቸው አባባል “በዩክሬን ውስጥ ለሚደረግ ረጅም ጦርነት እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን” ብለዋል።
ምንም እንኳን የኔቶ ወታደራዊ ጥምረት ለዩክሬን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለወታደራዊ አቅም ግንባታ እርዳታ ቢሰጥም ፥ የኪየቭ መንግስት በሰኔ ወር በደቡብ እና በምስራቅ በሚገኙ የሩሲያ ግዛቶች ላይ የመልሶ ማጥቃት ከጀመረ በኋላ የሚጠበቀውን ያክል ስኬት እንዳላገኘ ተቺዎች ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ በቅርብ ቀናት ውስጥ በክራይሚያ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ከባድ የዩክሬን ጥቃቶች በሩሲያ የጦር መርከቦች እና ሚሳኤሎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። አቶ ስቶልተንበርግ በተጨማሪ በሰጡት አስተያየት የዩክሬን ወታደራዊ ስልቶች በሩሲያ ጦር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረዋል ብለዋል። ይህንንም ሲያብራሩ “ከመነሻው የሩስያ ጦር በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ጠንካራ የጦር አቅም ያላት ሃገር ነበረች ፥ አሁን ላይ ግን የሩሲያ ጦር በዓለም ሳይሆን በዩክሬን ውስጥ ሁለተኛው ጠንካራ ጦር ነው” ሲሉ የሩሲያን የማሸነፍ ዕድል በጥርጣሬ ገልፀዋል።
የኔቶ ሃላፊው በመቀጠል "ይህ በጣም አስደናቂ ነው ፥ ይህ እውን ሊሆን የቻለበት ምክንያት በዩክሬን ወታደሮች ድፍረት የተሞላበት ትግል፣ ፈቃደኝነት፣ ቁርጠኝነት እና አይበገሬነት ነው” ብለዋል። አክለውም “የሩሲያ ወረራ የካቲት 2014 ዓ.ም. በሙሉ አቅሙ አጠቃላይ ወረራ በፈፀመበት ጊዜ ፥ አብዛኛዎቹ የጦር ባለሙያዎች ኪየቭ በቀናት ውስጥ እንደምትወድቅ እና ዩክሬንም በሳምንታት ውስጥ በሩሲያ ቁጥጥር ስር እንደምትገባ ተናግረው ነበር ፤ ይህንንም ትንበያ ዩክሬናውያኑ ስህተት መሆኑን አረጋግጠዋል” ብለዋል።
የኔቶው ባለስልጣን አቶ ስቶልተንበርግ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እና ዩክሬናውያን ጦርነቱን ካቆሙ አገራቸው ዩክሬን እንደማትኖር አጥብቀው ይከራከራሉ።
በተጨማሪም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ሩሲያ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ካቆሙ ብቻ ፥ እንደሳቸው አባባል "ሰላም እናገኛለን" ብለዋል።
2014 ዓ.ም. የካቲት ወር ላይ የሩሲያ ወረራ ከጀመረ ወዲህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ተብሎ የሚታመንበት ደም አፋሳሹ ጦርነት አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
 

18 September 2023, 10:54