ፈልግ

ለከፍተኛ የአየር ንብረት አደጋ እና የአካባቢ ክስተቶች የተጋለጡ ልጆች ለከፍተኛ የአየር ንብረት አደጋ እና የአካባቢ ክስተቶች የተጋለጡ ልጆች  (ANSA)

በአየር ንብረት ቀውሱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት 2ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ተፈናቅለዋል ተባለ

‘ሴቭ ዘ ችልድረን’ የተባለው የህፃናት አድን ድርጅት በድንገተኛ አደጋዎች መከላከል፣ ዝግጁነት፣ ድጋፍ እንዲሁም የአየር ንብረት አደጋዎችን የመከላከል ሥራዎችን ለማሻሻል እየሰራ ነው። በኬንያ ናይሮቢ እስከ ጳጉሜ 3 2015 ዓ.ም. ድረስ በሚካሄደው ለአህጉሪቱ የመጀመሪያው የሆነው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የዓለም መሪዎች ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጡ ይህ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጥሪውን አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በ 2014 ዓ.ም. ከሰሃራ በታች ያሉ የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ የአፍሪካ ህጻናት አጠቃላይ ቁጥር በእጥፍ ገደማ መጨመሩን በዓለም ዙሪያ ያሉ ተፈናቃዮችን የሚቆጣጠር እና መረጃን የሚሰጥ መንግስታዊ ያልሆነው የሀገር ውስጥ መፈናቀል ክትትል ማዕከል መረጃ ያሳያል ።
ከመቶ ዓመት በላይ በህፃናት ዙሪያ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራየሚገኘው ‘ሴቭ ዘ ችልድረን’ የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደገለፀው ቁጥሩ ከልክ በላይ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልገዋል ብሏል። በ 2014 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ቢያንስ 1.85 ሚሊዮን የሚሆኑ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ህጻናት በአየር ንብረት ቀውስ ሳቢያ በገዛ አገራቸው ተፈናቅለዋል ብሏል። የአየር ንብረት አደጋዎች በጤና ፣ በግብርና ፣ በፀጥታ ፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በሥራ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጅ ላይ ትልቁን የጤና መታወክን አደጋን እንደሚያስከትሉም አመላክቷል።

የናይጄሪያ እና ሶማሊያ የተጠቂዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ

በቦርኖ ግዛት እና በሌሎች የናይጄሪያ አካባቢዎች በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ጨምሯል። በዚህም ሳቢያ 427,000 የሚገመቱ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 854,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ሶማሊያ በአንፃሩ 6.6 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቂ ያደረገ አምስት የዝናብ ወቅቶችን በማጣቷ ምክንያት 39% የሚሆነው ህዝቧ አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰ ረሃብ ውስጥ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ በ1.1 ሚሊዮን በሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
እነዚህ አሳሳቢ ቁጥሮች በአየር ንብረት ቀውስ እና በአስከፊ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ሳቢያ የህጻናት ህይወት በክልሉ ውስጥ እንዴት በአደጋ እየተጎዳ እንደሆነ ሴቭ ዘ ችልድረን የገለጸ ሲሆን ፥ ምንም እንኳን የአፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ብክለት መንስኤዎች ዝቅተኛውን ድርሻ ቢይዙም በይበልጥ እየተጎዱ ያሉት ግን እነሱ ናቸው ብሏል።

"የአየር ንብረት ስደተኞች" ቁጥር እያደገ ነው

ሴቭ ዘ ችልድረን እንደገለጸው የኤልኒኖ የአየር ሁኔታ መከሰቱ ለከፋ የሚቲዎሮሎጂ ክስተት አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ እና ዘንድሮ የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች ቁጥርን ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል። በ 2014 ዓ.ም. በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በሚገኘው የቦርኖ ግዛት በጎርፍ አደጋ ከ30,000 በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
ፋልማታ ተብላ የምትጠራው የ13 ዓመቷ ልጅ ልምዷን እንዲህ ስትል ተናግራለች “ሕይወት ከባድ ነበር ፥ ከቤተሰባችን አባላት ስለተለያየን ስለነሱ አንዳች ነገር ሰምተን አናውቅም ፥ እዚህ ከመጣን በኋላ ለመጠለያ የሚሆን ትንሽ ክፍል አግኝተናል ፥ ነገር ግን የመጠልያው አሰራር በጣም መጥፎ ነበር። ምክንያቱም በዝናብ ተበላሽቶ ነበርና ፥ ጣሪያውም በጣም ያፈሳል ፥ አንዳንድ የክፍሉ በሮችም ክፍት ናቸው ፥ ደመናውን ሳይ እፈራለሁ ምክንያቱም የጎርፉን አደጋ ያስታውሰኛልና” ብላለች።

የህፃናት አድን ድርጅቱ ጥሪ

በኬንያ ናይሮቢ ከነሃሴ 29 - ጳጉሜ 3 2015 ዓ.ም. እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ልምዳቸውን እያካፈሉ እና ስጋታቸውንም እየገለጹ ይገኛሉ።
በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ የሴቭ ዘ ችልድረን ክልላዊ ጽህፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ፣ ዘመቻ እና ሚዲያ ዳይሬክተር የሆኑት ቪሽና ሻህ እንደተናገሩት “ፋልማታ ባለፈው ዓመት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያጋጠማት የህይወት ልምድ አብዛኛው ህፃናት ላይ የደረሰ ነው” ያሉ ሲሆን ፣ "በናይጄሪያ እና በአካባቢው ብዙ ህጻናት በስጋት ውስጥ እንዳሉ እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ለሰብሎች መበላሸት አልፎም ቤቶታቸውን እያወደመ ስለሆነ ፥ ከአንዱ አደጋ ሲሸሹ ሌላኛው ስላለመከሰቱ እርግጠኛ ባለመሆናቸው በሕይወት ስለመቆየታቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ናቸው” ብለዋል። ሃላፊው በማከልም “እነኚህ ህፃናት ይህ ቀውስ እንዲፈጠር ያደረጉት ምንም አስተዋጽኦ ዬለም” በማለት ተናግረዋል። ልጆቹ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ቀውስን ለመከላከል እና በፋይናንስ ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነትን እንዲያከብር ይፈልጋሉ ፥ ጥፋትን እና ጉዳቶችን ለመቅረፍ ብሎም የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል።
ለህጻናት ቤታቸውን ማጣት ማለት የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት ፣ ምግብ እና ደህንነትን ማጣት ማለት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ቀውሱን ለመዋጋት የህፃናት አድን ድርጅቱ ስራ ህጻናትን እና ማህበረሰባቸውን ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ አደጋዎች ለመከላከል ፣ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እና ለማገገም ድጋፍ ማድረግን ያጠቃልላል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በሁሉም ክልሎች ትንበያዎችን እና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በንቃት ይከታተላል፣ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ማህበረሰቦች ሊከሰቱ የሚችሉትን መጥፎ ተጽዕኖዎች ለመተንበይ ፣ ለመዘጋጀት እና ለመከላከል ይረዳል።
 

06 September 2023, 15:41