ፈልግ

በስፔን የታየው ድርቅ በስፔን የታየው ድርቅ  (ANSA)

ዓለማችን በከፍተኛ የውሃ እጥረት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ተገለጸ

የዓለም ሃብት ኢንስቲትዩት ተብሎ የሚጠራ ድርጅት ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት፥ ዓለማችን በከፍተኛ የውሃ እጥረት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጾ፥ ሁኔታው ሊባባስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።ማዕከሉ በሪፖርቱ የውሃ ፍላጎት መጨመር እና የአየር ንብረት ቀውስ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ እንደፈጠረ ገልጾ፥ ቀውሱ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አገራት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በየዓመቱ አንድ አራተኛው የዓለምን ሕዝብ እጅግ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥመው የገለጸው የዓለም ሃብት ማዕከል በአራት ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚያወጣውን ሪፖርት ነሐሴ 10/2015 ዓ. ም. ይፋ አድርጓል። ማዕከሉ በሪፖርቱ እንደገለጸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2050 ዓ. ም. ቀደም ሲል በውሃ እጥረት ከተጎዱት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በውሃ ቀውስ እንደሚጠቁ አስጠንቅቋል። እጅግ ከፍተኛ የውሃ እጥረት የሚታይባቸው አንዳንድ አገሮች ያላቸውን የውሃ ሃብት መጠን በሙሉ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ሪፖርቱ ገልጾ፥ ባህሬንን፣ ቆጵሮስን፣ ኩዌትን፣ ሊባኖስን እና ኦማንን የአጭር ጊዜ ድርቅም ቢሆን ለውሃ መመናመን አደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል አስጠንቅቋል። 25 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ የሚወክሉ 25 አገራትን በየዓመቱ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው፥ ውሃ በዓለማችን ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም በበቂ ሁኔታ እንደማይመራ የጥናት ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ እና የዚህ ዓመት ሪፖርት አዘጋጅ ወ/ሮ ሳማንታ ኩዝማ ገልጸዋል። እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ ከ1960 ዓ. ም. ጀምሮ የዓለም የውሃ ፍላጎት ከእጥፍ በላይ መጨመሩን እና በ2050 ዓ. ም. ከ20-25 በመቶ እንደሚጨምር ሪፖርቱ ተንብዮ፥ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ እንደ ግብርና ያሉ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች ማደግ ለውሃ እጥረት ምክንያት መሆናቸው ገልጿል።

በውሃ እጥረት የተጠቁ አካባቢዎች

መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ በውሃ ዕጥረት የተጎዱ አካባቢዎች መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፥ በምዕተ-ዓመት አጋማሽ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ የፖለቲካ ግጭቶች በመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በኢንዱስትሪዎች ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ሪፖርቱ አመላክቷል። ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት ለውጥ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት እንደሚከሰትም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2050 ዓ. ም. በ163 በመቶ እንደሚጨምርም ሪፖርቱ አመላክቷል። የዘንድሮው ሪፖርት አዘጋጅ ሳማንታ ኩዝማ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ለቤት ውስጥ አገልግሎት እና ለመስኖ የውሃ ፍላጎት መጨመሩን ጠቁመው፥ በሌላ በኩል በውሃ እጥረት ከተጠቁ አንዳንድ ክልሎች በስተቀር በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ውስጥ የውሃ ፍላጎት የተረጋጋ መሆኑን ገልጸዋል።

የውሃ ቀውስን ለማስወገድ የተወሰዱ እርምጃዎች

የአየር ንብረት ለውጥ የውሃ ቀውስ እንዳባባሰው የገለጸው ሪፖርቱ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በውሃ ላይ ተጽዕኖን በማሳደር በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን በቀጥታ እንደሚጎዳ ዓለም አቀፍ የምግብ፣ የደን፣ የውሃ እና የውቅያኖስ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ቻርለስ አይስላንድ ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ድርቅ እና ሙቀት ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ በማድረግ  በውሃ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖን እንደሚያሳድር ገልጸው፥ የውሃ እጥረት ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ እንደሚጥል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 13/2015 ዓ. ም. በተከበረው የዓለም የውሃ ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ውሃ ለብክነት፣ ለጉስቁልና ወይም ለጦርነት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል፥ ነገር ግን ለጥቅማችን እና ለመጪው ትውልድ ጥቅም ተጠብቆ ሊቆይ ይገባል” ብለዋል ። እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፥ እንደ ላስ ቬጋስ እና ሲንጋፖር ያሉ ከተሞች የውሃ ሃብቶችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ለእፅዋት ማዋል እንደሚቻል አሳይተዋል። ከውጤቱ አንፃር ድርጊቱ የዘገየ ቢመስልም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅ ለውሃ ቀውስ እንደገና መዳረጉን ሪፖርቱ አስታውሳል።

 

17 August 2023, 17:20