ፈልግ

በሄይቲ ያለውን የጸጥታ ችግር በመቃወም ወደ ጎዳና የወጡ ሰልፈኞች በሄይቲ ያለውን የጸጥታ ችግር በመቃወም ወደ ጎዳና የወጡ ሰልፈኞች  (ANSA)

በሄይቲ በተቀሰቀሰው አመጽ 300 ሴቶች እና ህጻናት መታገታቸው ተነገረ

በሂይቲ ውስጥ ሰዎችን ማገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” አስታወቀ። ዘንድሮ ከጥር እስከ ሰኔ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሦስት መቶ ሕጻናት እና ሴቶች መታገታቸውን ድርጅቱ የገለጸ ሲሆን፥ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች የካሪቢያን አገር በሆነች ሄይቲ ውስጥ ጸጥታ በመፍረሱ ምክንያት ተቃውሟቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጸጥታ እጦት እና በዓመፅ ውስጥ በምትገኝ ሄይቲ ውስጥ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርስ አፈና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን የህጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” አስታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ 300 ህጻናትና ሴቶች በሕገወጥ ታጣቂዎች መታገታቸው  የተረጋገጠ ሲሆን፥ ይህም ካለፈው ዓመት አጠቃላይ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን እና ከ 2021 በሦስት እጥፍ መብለጡን ድርጅቱ አስታውቋል።

ሴቶች እና ህፃናት በታጠቁ ቡድኖች ተወስደዋል

ብዙውን ጊዜ ለገንዘብ ወይም ለሌሎች ዘዴዎች ሲባል ሄይቲ ውስጥ ህጻናት እና ሴቶች በታጣቂዎች በግዳጅ እንደሚወሰዱ የገለጸው የ “ዩኒሴፍ” ዘገባ፥ አምልጠው ወደ መኖሪያቸው መመለስ የቻሉ ተጎጂዎች ብዙ ዓመታትን ሊቆዩ በሚች ጥልቅ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጠባሳዎች እንደሚሰቃዩ አስታውቋል። የአካባቢው የጤና ሥርዓቶች ሊፈርሱ መድረሳቸውን እና ትምህርት ቤቶችም ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን የዘገበው የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አክሎም፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ብጥብጥ፣ ዘረፋ፣ መንገድ መዝጋት እና የታጠቁ ቡድኖች መስፋፋት የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥረቶችን በእጅጉ በመገደቡ፥ አስፈላጊውን ዕርዳታ ለተጎጂ ማኅበረሰቦች ማከፋፈል አዳጋች መሆኑን አስታውቋል።

ወራት በጨመሩ ቁጥር ፍርሃትም እየመጨመረ መምጣቱ፥ ሁኔታው ቀድሞም ቢሆን አስቸጋሪ በሆነበት አካባቢ ዕርዳታን በሚያከፋፍሉ ሰዎች ላይ ጫናን መፍጠሩ ታውቋል። “ሁኔታው በአጠቃላይ ጥፋት የበዛበት ነው” በማለት የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ”፥ እስካሁን ድረስ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናትን ጨምሮ በ 5.2 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች፣ ይህም ማለት ከጠቅላላው የሄይቲ ሕዝብ መካከል ግማሽ ያህሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

“ዩኒሴፍ”፥ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች አደጋ ላይ ናቸው

በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን አገራት የ “ዩኒሴፍ” ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌሪ ኮኒል፥ “ከሥራ ባልደረቦቻችን የምንሰማቸው ታሪኮች አስደንጋጭ እና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው" በማለት መግለጫው ሰጥተዋል። የ “ዩኒሴፍ” ተወካዩ፥ "በአገሪቱ ውስጥ የጠለፋ እና የአፈና ድርጊት መጨመሩ በጣም አሳሳቢ ነው” ብለው፥ ታጣቂዎቹ የሄይቲን ሕዝብም ሆነ እነርሱን ለመርዳት እዚያው የሚገኙት የዕርዳታ ሠራተኞችን በማስፈራራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ በዚህ መካከል በሄይቲ ሕጻናት፣ ሴቶች እና ቤተሰቦች መካከል ያልተለመደ ከፍተኛ ጽናት መኖሩን እና በፈተናዎች መካከል ተስፋ የማይቆርጡ መሆናቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል። ተወካዩ በማከልም፥ “የሕዝቡ ድፍረት እያደገና ሊታሰብ ወደማይችል ሽብር ውስጥ ሊደርስ ስለሚች፥ የሽብር ጥቃቱ ከወዲሁ መቆም አለበት” ብለው፥ ከዚህ እውነታ አንጻርም፥ በሄይቲ ውስጥ የታፈኑ ህጻናት እና ሴቶች በሙሉ በአስቸኳይ ተፈተው በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የህጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” ጠይቋል።

ዓለም አቀፍ ጣልቃገብነት

በሄይቲ እያሽቆለቆለ በመጣው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ሰኞ ሐምሌ 30/2015 ዓ. ም. በሄይቲ መዲና ፖርት-አው-ፕሪንስ ጎዳናዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን በመግለጽ ከታጠቁ ወንበዴዎች ጥቃት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። የወሮበሎች ጥቃት የድሆችን ችግር በማባባሱ ሄይቲ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ኃይል የሚያሰማራበትን ውሳኔ እየጠበቀች መሆኗ ተነግሯል። የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት፥ እየጨመረ በመጣው ጥቃት እና ድህነት ምክንያት ወደ 73,500 የሚጠጉ ሰዎች ሄይቲን ለቀው መውጣታቸውን አስታውቋል።

ለቀውሱ ምላሽ መስጠት

ካጋጠሙት ግዙፍ ፈተናዎች ባሻገር፥ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድረጅት “ዩኒሴፍ” ለችግሩ ምላሽ መስጠቱን የቀጠለ ሲሆን፥ ድርጅቱ ከጠላፊዎች በሕይወት ለሚተርፉ ሕፃናት እና ተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሕይወት አድን ዕርዳታዎችን በማቅረብ፣ የሕክምና አገልግሎቶችን፣ ሥነ-ልቦናዊ ማኅበራዊ ድጋፎችን፣ ሕጻናት የፈውስ እና የማገገም ሂደቶችን የሚጀምሩበት ደህንነታቸው የተጠበቀ ቦታዎችን ለማረጋገጥ እየሠራ እንደሚገኝ ታውቋል።

10 August 2023, 12:52