ፈልግ

በፓኪስታን ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ንጹህ ውሃ አያገኙም። በፓኪስታን ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ንጹህ ውሃ አያገኙም።  (AFP or licensors)

በፓኪስታን ውስጥ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ ተከትሎ በፓኪስታን የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ያለ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እየኖሩ እንደሆነ እና እነዚህ “ለችግር የተጋለጡ ህጻናት” በጎርፍ በተጎዱ አካባቢዎች ያለ መሰረታዊ አቅርቦቶች እየኖሩ እንደሚገኙ ዩኒሴፍ የተባለው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት ማስጠንቀቂያውን ልኳል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዚህ ዓመት ከውቅያኖስ በሚነሳ አውሎ ንፋስ የቀላቀለው ከባድ ዝናብ በመላው ፓኪስታን የ87 ህጻናትን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ፥ ከባለፈው ዓመት የጎርፍ አደጋ ገና እያገገሙ የሚገኙትን የማህበረሰብ ክፍል ችግር ይበልጡኑ እንዳባባሰውም ተነግሯል።
እንደ የፓኪስታኑ ዩኒሴፍ ዘገባ ከሆነ ፥ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ወረዳዎች ሕይወት አድን የሆነ የምግብ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።
ባለፈው ነሃሴ 19 2015 ዓ.ም. ዩኒሴፍ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት ሰብአዊ እርዳታ እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል” ሲል የማስጠንቀቂያ መልዕክትም አውጥቷል።
የጎርፍ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከግማሽ በላይ ህፃናት የሆኑበት ከ8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ንፁህ ውሃ ሳያገኙ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቱ ገልጿል።
ፓኪስታንን ብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድታውጅ ያስገደደው የጎርፍ አደጋ ከአንድ ዓመት በኋላም ቢሆን እስካሁን ድረስ እየተሠሩ ያሉት የማገገሚያ እና የማቋቋሚያ ጥረቶች የገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው ተነግሯል። ዩኒሴፍ የህይወት አድን ድጋፍ ለማድረግ 173.5 ሚሊዮን ዶላር ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፥ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገው ግን 57 በመቶው ብቻ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የፓኪስታን ልጆች ተረስተዋል

በፓኪስታን የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት አብዱላህ ፋዲል በሰጡት መግለጫ “በጎርፍ በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ለአደጋ የተጋለጡ ህጻናት አስከፊ ዓመት እያሳለፉ ይገኛሉ" ብለዋል።
'ህፃናት ልጆቹ በጣም የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ተነጥቀዋል ፥ ቤታቸውን እና ትምህርት ቤታቸውን አጥተዋል። በዚህ ላይ አውሎንፋስ የቀላቀለው ዝናብ ሀገሪቱን እንደገና ሲመታ ፥ የአየር ንብረት አደጋ ስጋት በህዝቡ ዘንድ መንሰራፋቱን ቀጥሏል' ብለዋል።
አቶ ፋዲል እንደሚናገሩት “የማገገሚያ ጥረቱ ቀጥሏል ፥ ነገር ግን ሁሉንም ማዳረስ አልተቻለም ፥ ይህ በዚህ ከቀጠለ የፓኪስታን ህፃናት የመረሳት አደጋ ሊጋረጥባቸው ይችላል” ብለዋል።

ውሃው ሊቀንስ ይችላል ፥ ነገር ግን ችግሮቹ ይቀጥላሉ

ባለፈው ዓመት ላይ 33 ሚሊዮን ህዝብን ያጠቃው ጎርፍ ፥ የሀገሪቱን አንድ ሶስተኛውን በማጥለቅለቅ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን እና የውሃ ዝርጋታዎችን ጨምሮ ጠቃሚ መሠረተ ልማቶችን አውድሟል።
የጎርፍ አደጋው ከመከሰቱ በፊትም ብዙ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ነበሩ ፥ አልፎ ተርፎም የተመጣጠነ ምግብ እጦት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ እና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የአከባቢ የንፅህና አጠባበቅ በጣም ዝቅተኛ ሁኔታ ውስጥ ነበር።
ዩኒሴፍ እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ በመገምገም የፓኪስታን መንግስት እና አጋሮቹ መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለልጆች እና ቤተሰቦች ማቅረብን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል። የፍትሃዊነት ክፍተቶችን ለመቅረፍ እና ለአየር ንብረት አደጋዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ ፥ ለአየር ንብረት አደጋዎች ዝግጁነትን መገንባት ወይም ማደስ አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል።
የፓኪስታንን ልጆች መርሳት አንችልም ፥ የጎርፍ ውሃው አልፏል ፥ ነገር ግን በዚህ የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት በሚታይበት ክልል ውስጥ ችግራቸው አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው” ብለዋል አቶ ፋዲል።

የዩኒሴፍ የማዳረስ ጥረቶች

ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተገኘ ድጋፍ ዩኒሴፍ እና አጋሮቹ ከነሃሴ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎቶችን ለ3.6 ሚሊዮን ሰዎች ማዳረስ ችለዋል።
የውሃ መስመሮች በተበላሹባቸው አካባቢዎች ለ1.7 ሚሊዮን ሰዎች የንፁህ ውሃ አቅርቦት መልሶ ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ወደ 545,000 የሚጠጉ ህጻናት እና ተንከባካቢዎች የአእምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ድጋፍ አግኝተዋል።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዩኒሴፍ 2.1 ሚሊዮን ህጻናት ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደተጋረጡ በምርመራ ያረጋገጠ ሲሆን ፥ ከነዚህም ከ172,000 በላይ ህጻናት ህይወት አድን ህክምና ለማግኘት ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች መግባታቸው ታውቋል።
ሆኖም ከጎርፍ አደጋው ተጽእኖዎች የማገገም ፍላጎቶች ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት ከሚያስፈልጉት ሀብቶች መብለጣቸውን ቀጥለዋል።
 

28 August 2023, 12:45