ፈልግ

የነዳጅ ድጎማ መነሳቱን እና የኑሮ ውድነትን በመቃወም በሌጎስ ታላቅ ተቃውሞ ሲደረግ የነዳጅ ድጎማ መነሳቱን እና የኑሮ ውድነትን በመቃወም በሌጎስ ታላቅ ተቃውሞ ሲደረግ  (ANSA)

ናይጄሪያ ታጣቂዎች በገበሬዎች ላይ በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት በምግብ እጥረት ስጋት ውስጥ ናት ተባለ

በገበሬዎች ላይ የታጠቁ ሃይሎች በሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና በምግብ እጥረት ስጋት ምክንያት ብዙ ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ሲሆን ፥ ይሄም በናይጄሪያ ላይ ከፍተኛ ስጋት እና ተቃውሞን እየፈጠረ ይገኛል። ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው ህፃናት አድን በጎ አድራጎት ድርጅት አስፈላጊውን እርዳታ፣ አገልግሎቶችን እና መሰረታዊ ነገሮችን በማቅረብ ለመርዳት እየሞከረ ነው።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በናይጄሪያ ገበሬዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሁን ያለውን የምግብ እጥረት ችግር አባብሶታል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የታጠቁ የሽብር ቡድኖች 147 ገበሬዎችን የገደሉ ሲሆን ፥ በሰሜን ምስራቅ የናይጄሪያ ግዛት በሆኑት ቦርኖ ፣ አዳዋማ እና ዮቤ ሞላይ ከተሞች ላይ ደግሞ በርካቶችን በማፈን ወስደዋል ተብሏል።
የናይጄሪያ አርሶ አደሮች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ኗሪዎቹ ከመኖሪያ አከባቢያቸው እና ከንግድ ቦታቸው ይፈናቀላሉ ፥ ይሄ ደግሞ የገቢ ምንጫቸውን እንዲያጡ ስለሚያደርጋቸው አከባቢያቸውን እየለቀቁ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተሰደዱ ይገኛሉ።
ከ3,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የብሔራዊ ድንገተኛ አደጋ መከላከል ኤጀንሲ የገለጸ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ደግሞ ወድመዋል ብሏል።
ቡልማ የተባለ ናይጄሪያዊ ገበሬ ስለ ታጣቂዎቹ ሲናገር “ያመረትናቸውን የግብርና ምርቶች እንዳለ ወስደውብን ነው የሄዱት ፥ በዚህም ምክንያት ባዶዋችንን ስለቀረን ለልጆቻችን ወደ ቤት የምንወስደው አንዳች ነገር ዬለንም” ያለ ሲሆን ፥ ቡልማ በማከልም "በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ አብዛኞቻችን በረሃብ እየተሰቃየን ያለነው ታጣቂዎቹ የእርሻ መሬቶቻችን ላይ በአግባቡ እንዳናርስ ስላደረጉን እና ይሄንንም ችለን ህይወታችንን ለአደጋ አጋልጠን በአከባቢያችን ብንቆይ እንኳ ያለንን ሁሉንም ነገር ሰርቀውብን ለረሃብ እንድንጋለጥ ዳርገውናል” በማለት በምሬት ይናገራል።
የቡልማ ስራ ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም ፥ ይሄን ማድረግ ቢያቆም ልጆቹ በረሃብ ሊሞቱ ስለሚችሉ በራሱ ላይ ወስኖ በአከባቢው ሊቆይ ተገዷል።

የናይጄሪያ በረሃብ የመመታት ስጋት

ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 25 ሚሊዮን ናይጄሪያውያን በረሃብ ሊጠቁ እንደሚችሉ ከተባበሩት መንግስታት ህፃናት አድን ፈንድ ዩኒሴፍ የወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ።
ሴቭ ዘ ችልድረን በበኩሉ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን የምግብ ፣ ንፁህ ውሃ ፣ አልሚ ምግቦችን እና የጤና አገልግሎቶችን በማቅረብ የእርዳታ እጁን ዘርግቷል። ከዚህም በተጨማሪ ለፖሊሲ ማስተካከያ እና ማሻሻያ በተለይም በማህበራዊ ደህንነት ፣ በጤና ዘርፍ እና በትምህርት ነክ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመንግስት የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ።
ይህን አሳሳቢ የምግብ እጥረት ቀውስን ለመግታት የህዝቡን ፍላጎት በማስቀደም እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የህጻናት አድን ድርጅት አስታውቋል።
ድርጅቱ በማከልም በአርሶ አደር ቤተሰቦች ላይ ጥቃት መውሰዳቸውን በቀጠሉ ከነዚህ ታጣቂ ድርጅቶች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት መታደግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ብሏል።
 

08 August 2023, 14:31