ፈልግ

በናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የመታሰቢያ ጸሎት ሲደረግ በናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የመታሰቢያ ጸሎት ሲደረግ  (ANSA)

የጃፓን እና የአሜሪካ ጳጳሳት ከኒውክሌር ነጻ ለሆነች ዓለም ያላቸውን አጋርነት ገለፁ

አምስት የጃፓን እና የአሜሪካ ጳጳሳት ምድራችን “ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ የሆነች ዓለም” እንድትሆን በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል። እ.አ.አ. ነሀሴ 2025 የሂሮሺማ እና የናጋሳኪ 80ኛ ዓመት የአቶሚክ ቦምብ ጥቃትን የሚያስታውስ መርሃ ግብር ላይ ተጨባጭ ማሻሻያዎች እንዲደረጉም ጥሪ አቅርበዋል

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. ነሐሴ 9 ቀን 1945 በናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ የፈነዳበት 78ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ አምስት በአቶሚክ ጦር መሳሪያ ጥቃት ከተፈፀመባቸው አካባቢዎች የተውጣጡ የጃፓን እና የአሜሪካ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ቡድን “የኑክሌር መሳሪያ የሌለበት ዓለም” ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ላይ በተጨባጭ ለመስራት ቃል ገብተዋል።

ወደ ጃፓን የሚደረግ መንፈሳዊ የሰላም ጉዞ

የጋራ የትብብር ሰነዱ ላይ የናጋሳኪ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ፒተር ሚቺያኪ ናኩሙራ፣ የሂሮሺማ ጳጳስ የሆኑት አሌክሲስ ሚትሱሩ ሺራሃማ ፣ የናጋሳኪ ሊቀ ጳጳስ ጆሴፍ ሚትሱኪ ታካሚ ፣ የሳንታ ፌ (ኒው ሜክሲኮ) ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ጆን ዌስተር እና የሲያትል (ዋሽንግተን) ሊቀ ጳጳስ በሆኑት ኢቲየን ፖል ፈርመዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ ወደ ማጠቃለያ የመጣው እ.አ.አ. 1945 በጃፓን የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት መታሰቢያ ለማክበር ሁለቱ የአሜሪካ ሊቃነ ጳጳሳት ከነሐሴ 1 እስከ 9 ወደ ጃፓን ባደረጉት የሰላም ጉዞ ወቅት ላይ ነው።
ሁለቱም የአሜሪካ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት እና ማሰማራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ባላቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን ፥ አሜሪካ ዋና ዋና የኒውክሌር ጦር ኃይሏን በምእራብ ዋሽንግተን ግዛት እና በኒው ሜክሲኮ ሳንታ ፌ የሚገኝበት እና የአቶሚክ ቦምብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራበት ቦታ ተደርጎም ስለሚወሰድ ነው።
በመንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ወቅትም ሁለቱ የአሜሪካ ሊቀ ጳጳሳት በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቶቹ ላይ የተሳተፉ ሲሆን የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዓለም መሪዎች የተደረገ ጥሪ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የኑክሌር ጦር መሣሪያን “ባለቤትነትን” ያወገዙበትን በማስተጋባት የዓለም መሪዎች የኑክሌር ጦር መሣሪያን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የተለየ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
ጥሪያቸው በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች ውጤቱ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጠባሳ ያለው መሆኑን ማሳወቅን እና የዩራኒየም ማዕድን ማውጣት እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ማምረት አካባቢ ላይ ያለውን ተፅእኖን መቀበልን ያጠቃልላል። አዳዲስ የጦር መሳሪያ ምርት ውድድርን ለመከላከል ውጤታማ ቁርጠኝነት፣ ከኑክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም መከላከል እና የኑክሌር ትጥቅ ማስፈታትን ለማራመድ እንዲሁም በኒውክሌር ጦርነትን ማንም አሸናፊ ሊኖር እንደማይችል እና ፈጽሞ የኒኩለር ጦርነት መካሄድ እንደሌለበት በድጋሚ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ነው።

ተጎጂዎችን ማስታወስ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. ህዳር 24 ቀን 2019 በሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት ጳጳሳቱ “የተጎዱትን በማሰብ ፣ በአንድነት ለመራመድ እና ለመጠበቅ” በሚል መንፈስ የሚወስዷቸውን ተጨባጭ ተግባራት ዘርዝረዋል።
ጳጳሳቱ ያለፈውን ጊዜ አስከፊነት ለማስታወስ እርስ በእርስ ለመሰማማት እና ውይይት ለማድረግ ያሰቡት ከሁለቱም ወገኖች በኩል ባሉ ተጠቂዎች ጋር ማለትም የሂሮሺማ እና የናጋሳኪ ተጠቂዎች፣ የዩራኒየም ማዕድን አውጪዎች፣ የሰላም ታጋዮች፣ የኒውክሌር መሐንዲሶች፣ የጦር ኃይሎች እና ዲፕሎማቶች ጋር እንደሆነም ታውቋል።

አብሮ መጓዝ

አብረው ለመጓዝ ፥ አምስቱ ጳጳሳት የኑክሌር የጦር መሣሪያ ለሌለበት ዓለም ለመመስረት ልዩ ዓላማ ያለው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የሥርዓተ ቅዳሴ መርሃግብር እንደሚኖራቸው የገለጹ ሲሆን ፥ በተቻለውም ሁሉ የኑክሌር ተጎጂዎችን ለመደገፍና በኑክሌር የተበላሹ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ልዩ የገቢ ማሰባሰብያ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

መከላከል

በመጨረሻም የኑክሌር የጦር መሳሪያ ጦርነትን ለመከላከል ፈራሚዎቹ ሀገራት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ክልከላ ስምምነትን እንዲፈርሙ እና የዓለም መሪዎች ለልማት እና እንክብካቤ የሚውለውን ገንዘብ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦችን ለመርዳት እና የአካባቢ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲያውሉ የድጋፍ ቅስቀሳቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
እስካሁን በመጀመሪያ ላይ በቅድስት መንበር የተፈረመው የስምምነት ሰነዱ ላይ አሜሪካ ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና እንግሊዝን ጨምሮ የቡድን ሰባት (G7) አገሮች አንዳቸውም አልፈረሙም።
አምስቱ የአሜሪካ እና የጃፓን ጳጳሳት ሌሎች ሀገረ ስብከቶች እና ሃይማኖታዊ ተቋማት በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ እንዲተባበሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
“የሰላሙ ልዑል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፥ አጋራችንና የጉዞው ባልደረባችን አጋርነታችንን ይባርክልን” በማለት እና “የሰላም ንግሥት የሆነችዉን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት” በመጠየቅ መግለጫቸውን አጠቃለዋል።
 

15 August 2023, 09:04