ፈልግ

የአፍጋን ሴቶች ባካቡል ጎዳናዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የአፍጋን ሴቶች ባካቡል ጎዳናዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ 

የአፍጋኒስታን ሴቶች በየቤቶታቸው የሚታሰሩበት ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ።

በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚደረጉ የመብት ጥሰቶች እና ተፅእኖዎችን አስመልክተው ከወጡት ፖሊሲዎች ውስጥ በውጭ አገራት የመማር መብትን የሚከለክለው እና በሃገሪቱ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችን የመጎብኘት እገዳውን አስመልክተው የወጡት ፖሊሲዎች የቅርብ ጊዜውን ክልከላዎችን ይወክላሉ። በሂዩማን ራይትስ ዎች የሴቶች መብት ክፍል ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ “እያንዳንዱ ግድግዳዎች ደረጃ በደረጃ በሴቶች ላይ እንዴት እንደሚዘጉ እና እያንዳንዱ ቤት ለሴቶቹ እስር ቤት እየሆነ የመጣበትን መንገድ ያመላክታል” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ወደ 100 የሚጠጉ የአፍጋኒስታን ልጃገረዶች ለትምህርት ወደ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እንዳይጓዙ በአካባቢው የታሊባን ባለስልጣናት መከልከላቸውን በዱባይ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚደግፈው ተቋም ኃላፊ ባለፈው ረቡዕ ዕለት ስለ ጉዳዩ አሳሳቢነት ተናግረዋል።
በኤክስ (ትዊተር) ላይ በወጣ ቪዲዮ የአል ሀብቶር ግሩፕ መስራች ሊቀመንበር የሆኑት ኻላፍ አህመድ አል ሀብቶር እንደዘገቡት “የታሊባን መንግስት እዚህ ዱባይ በእኔ ስፖንሰር ተደርገው ለመማር የሚመጡትን አንድ መቶ ልጃገረዶችን እንዴት እንደከለከላቸው እና ሙሉ በሙሉ በተከፈለበት የአውሮፕላን ጉዞ እንዳይሳፈሩም አድርጓል” በማለት ከገለጹ በኋላ አክለውም “እኛ እዚህ ዱባይ እንደ መጠለያ ፣ ትምህርት ፣ የትራንስፖርት ደህንነት እና የመሳሰሉትን ሁሉንም ነገር አዘጋጅተናል” ሲሉ አብራርተዋል።

የጉዞ ገደቦች

ቢቢሲ የ20 ዓመቷን አፍጋኒስታን ተማሪ ቤተሰቦቿን ተሰናብታ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ከተጓዘች በኋላ የታሊባን ባለስልጣናት ትኬቷን እና የተማሪ ቪዛዋን እንዳዩ እንዴት እንደከለከሏት ምስክርነቷን አቅርቧል።
"ሴት ልጆች በተማሪ ቪዛ ከአፍጋኒስታን መውጣት አይፈቀድላቸውም ብለውኛል” ስትል ተናግራለች። በታሊባን ፖሊሲዎች መሰረት ሴቶች በራሳቸው ወደ ውጭ አገር እንዳይጓዙ የተከለከሉ ሲሆኑ ፥ ይህን ፍቃድ ለማግኘት “ከባሎቻቸው ወይም ተዛማጅ ወንድ ጓደኛቸው እንደ ወንድም፣ አጎት ወይም አባት፣ ‘ማህራም’ በመባል የሚታወቁ ወንድ አጃቢዎች ጋር መያያዝ አለባቸው” ሲል ቢቢሲ ጽፏል።
ነገር ግን ልጅቷ እንደገለጸችው ‘ማህራም’ የነበራቸው ሌሎች ሶስት ሴት ተማሪዎች በአውሮፕላኑ ውስጥ ገብተው የነበሩ ቢሆንም ምክትል እና የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ከአውሮፕላኑ አውርደዋቸዋል” ስትል ስለ ታሊባን ባለስልጣናት ድርጊት አጋልጣለች።

ባንድ-ኢ-አሚር ብሔራዊ ፓርክ

የአፍጋኒስታን ምክትል እና የበጎ አድራጎት ተጠባባቂ ሚኒስትር የሆኑት መሀመድ ካሌድ ሃናፊ ሴቶች በጣም ታዋቂ ከሆኑ መስህቦች አንዱ የሆነውን እና የሀገሪቱ የመጀመሪያ ብሄራዊ ፓርክ የሆነውን በባሚያን ግዛት የሚገኘውን የባንድ ኢ-አሚር ብሔራዊ ፓርክን እንዳይጎበኙ ከልክለዋል።
እገዳውም ተፈፃሚ እንዲሆን የተደረገው የአፍጋኒስታን ሴቶች ሂጃብ የሚለብሱበትን ትክክለኛ መንገድ ባለመከተላቸው ነው ተብሏል።
ዘ ጋርዲያን እ.አ.አ. በ2013 የባንድ ኢ-አሚር ብሄራዊ ፓርክ አራት ሴቶችን የፓርኩ ጠባቂ አድርጎ ከቀጠረ በኋላ እርምጃው በሃገሪቷ ውስጥ ከዚህን በፊት ተከስቶ የማያውቅ እና ‘የለውጥ ምልክት’ እንደሆነ ዘግቦ ነበር።

"ግድግዳዎቹ ተዘግተዋል"

በሂዩማን ራይትስ ዎች የሴቶች መብት ክፍል ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ሄዘር ባር “እያንዳንዱ ግድግዳዎች ደረጃ በደረጃ በሴቶች ላይ እንዴት እንደሚዘጉ እና ይሄም እያንዳንዱ ቤት ለሴቶቹ እስር ቤት እየሆነ የመጣበትን መንገድ ያመላክታል” በማለት አረጋግጠዋል።
የሰብአዊ ድርጅቱ እገዳውን በአፍሪካ ሴቶች ላይ በተጣለ ሰፊ የእገዳ እና የክልከላ ማዕቀፍ ውስጥ የገባው ታሊባን ነሐሴ 9 2013 ዓ.ም. አፍጋኒስታን ውስጥ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ በተደረገው የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከሰጠው ማረጋገጫ ጋር እንደሚፃረር ገልጿል።
“ሴቶች በእኛ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲማሩ እና እንዲሰሩ እንፈቅዳለን ፥ በዚህም ሴቶች በህብረተሰባችን ውስጥ በጣም ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ” ሲል ታሊባን በወቅቱ ተናግሮ ነበር።

የአፍጋኒስታን ሴቶች ሰብአዊ መብቶች

ቢቢሲ ከመስከረም 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የአፍጋኒስታንን ሴቶች መብት ቀስ በቀስ እየተጨፈለቀ ያለበትን አጠቃላይ እይታ ከመረመረ ከአንድ ወር በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሴቶች ምንም ዓይነት መብት በመንፈግ ለወንዶች ብቻ መከፈታቸውን የሃገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል ።
ይህን በመቃወም በአፍጋኒስታን ከተሞች አውራ ጎዳናዎች ላይ የተካሄዱትን ሰልፎችን በኃይል ለማስቆም ተሞክሯል ፥ ሆኖም እገዳዎች ቀስ በቀስ እየጨመሩ ነው። አሁን ለትክክለኛዎቹ ፖሊሲዎች ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ሊወሰድ በሚችለው ታህሳስ 2013 ዓ.ም. በወጣው ህግ መሰረት ሴቶች ከ 72 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የጉዞ ርቀቶችን ከቅርብ ወንድ ዘመዶቻቸው ጋር ብቻ እንዲጓዙ ይደነግጋል ሲሉ ምክትል የበጎ አድራጎት ሚኒስቴሩ በወቅቱ ተናግረዋል።

የአለባበስ ድንጋጌዎች

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 29 2014 ዓ.ም. የአፍጋኒስታን መንግስት የበላይ መሪ በሆኑት በሙላህ ሀይባቱላህ አኩንዛዳ የፀደቀ አዲስ ህግ አውጥቷል። በዚህም ህግ ሴቶች ከጭንቅላታቸው እስከ እግር ጣቶቻቸው ድረስ የሚሸፍን ልብስ እንዲለብሱ ይደነግጋል።
ቢቢሲ “ሴቶች ከህዝብ የቀን ተቀን የህይወት እንቅስቃሴ መጥፋት እንደጀመሩ እና የመስራት መብት ተነፍጓቸው ቤተሰቦቻቸውን የመመገብ አቅም እንዳጡ ፥ በዚህም ምክንያት ወደ ጎዳና ወጥተው ለልመና የተዳረጉ የሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ግልፅ እየሆነ መጥቷል” በማለት ዘግቧል።

በዩኒቨርሲቲዎች እና በህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች የተደረጉ እገዳዎች

ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም. ባሉ ጥቂት ወራት ውስጥ ሴቶች እንደ ስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ መዋኛ ገንዳዎች እና የህዝብ መታጠቢያዎች ካሉ የህዝብ ቦታዎች ታግደዋል። በታህሳስ 11 2014 ዓ.ም. የታሊባን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ተጨማሪ ማስታወቂያ እስከሚወጣ ድረስ በሁሉም የመንግስት እና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ለሴቶች የሚሰጥ ትምህርትን አግዶ ነበር።
ከአራት ቀናት በኋላ የታሊባን ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሴት ሰራተኞቻቸው ወደ ስራ መምጣታቸውን እንዲያቆሙ ወይም ፈቃዳቸው እንዲሰርዙ እንዲጠይቁ ትእዛዝ አስተላለፈ።
ይህ በእንዲህ እያለ በቅርቡ በሃምሌ 2015 ዓ.ም. “ሴቶች ከታሊባን መንግስት ተቆጣጣሪዎች ምርመራ ርቀው የሚሰበሰቡባቸው የመጨረሻዎቹ ጥቂት ቦታዎች” ተብለው የተገለጹ የውበት እና የፀጉር ሳሎኖች ተዘግተው 60,000 የሚሆኑ ሴቶችን ሥራ አጥ አድርጓል።

"ተለውጠናል"

ቢቢሲ በተጨማሪም ሴቶች በአሁኑ ጊዜ ገደብ ቢጣልባቸውም አሁንም ድረስ ወደ አፍጋኒስታን ማህበረሰብ ለመግባት እንዴት እየሞከሩ እንደሆነ ዘግቧል።
"በአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የምድር ውስጥ ሚስጥራዊ ትምህርት ቤቶች እየተሰሩ ነው። አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሁንም በራዳር ቁጥጥር ስር ሆነው መስራት የሚሞክሩ ሴቶችን ቀጥረው እያሰሩ ነው ፥ ሴቶችም የአመጽ ጭቆና እና የእስራት ስጋት ውስጥ ገብተውም ቢሆን አልፎ አልፎ በጎዳና ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው” በማለት ዘገባው ያትታል።
“ከ20 ዓመት በፊት ታሊባኖች ያፈኗቸው ሴቶች ጋር እኛ ተመሳሳይ አይደለንም ፥ እኛ ተለውጠናል ፥ ህይወታችንን አሳልፈን መስጠት ቢኖርብንም እንኳ ይሄን ሊቀበሉት ይገባል” ስትል አንዷ የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ ተናግራለች።
 

31 August 2023, 20:58