ፈልግ

በመካከለኛው ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በባህር ላይ ሞተዋል በመካከለኛው ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በባህር ላይ ሞተዋል 

ባህር አቋርጠው ለሚሰደዱ ስደተኞች ያለፈው ሳምንት አስጨናቂ ጊዜ ነበር ተባለ።

በመካከለኛው ሜዲትራኒያን አከባቢ በአደገኛ የስደተኞች የባህር ማቋረጫ መስመሮች ላይ የተነሳው ማዕበል በአሁኑ ሠዓትም ምንም የመቀነስ ምልክት እንዳልታየበት ተነግሯል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በበጋው ወራት ፥ ወትሮውኑ ባህር ላይ የሚነሱት ማዕበሎች ስለሚረጋጉ ፥ ህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞቹን በአውሮፓ የባህር ጠረፍ ወደሚገኙ መዳረሻዎች ለማጓጓዝ እድሉን ይጠቀሙበታል። ነገር ግን በጣም ያረጁ እና ለባህር ማጓጓዣነት የማይበቁ ጀልባዎችን በመጠቀም ለማቋረጥ መሞከሩ አደገኛ እና ብዙ ጊዜም መጨረሻው በአሳዛኝ ሁኔታ ያበቃል።
ባለፈው ሳምንት በቱኒዚያ በርካታ አሳዛኝ ክስተቶች ተከስተዋል። ነሃሴ 7/ 2015 ዓ.ም. ዕለተ ሰኞ በቱኒዚያ የባህር ዳርቻ ላይ የስደተኞች ጀልባ ተገልብጣ አስራ አንድ ሰዎች ሞተዋል። ብዙም ሳይቆይ በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት በላምፔዱዛ የባህር ዳርቻ ላይ ሌላ የስደተኞች ጀልባ በመስጠሟ ምክንያት በደረሰው አስከፊ አደጋ 41 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እያለ እነዚህ አደጋዎች ከተከሰቱ ሁለት ቀናት በኋላ ፥ ባለፈው ቅዳሜ ሌላ ጀልባ ተገልብጣ ሁለት ህጻናት ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ ከ1,800 በላይ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ መተላለፊያ መንገድ ተብሎ በሚታሰበው በሜዲትራንያን ባህር ላይ በጀልባ መገልበጥ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ፥ ባለፉት ሳምንታት የጣሊያን የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች በላምፔዱዛ ደሴት ውሀ ውስጥ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎችን መታደግ እንደቻሉም ተነግሯል።
ሰኔ 2015 ዓ.ም. ላይ በግሪክ የባህር ዳርቻ የስደተኞች ጀልባ ተገልብጣ በመስጠሟ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ ፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሳይገኙ ቀርተዋል።
በሌላው የዓለም ክፍልም በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ስደተኞች እንደሚሞቱ የሚታወቅ ሲሆን ለአብነትም ከምያንማር የፈለሱ የሮሂንጊያ ስደተኞችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ 17 ተሳፋሪዎች መሞተቸው እና ጀልባዋም አስቸጋሪዉን የባህር ላይ ጉዞ ስትጀምር ከ50 የሚበልጡ ሰዎችን አሳፍራ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይ መልኩ በሌላ ቦታ ቅዳሜ እለት በእንግሊዝ የመተላለፊያ መስመር አድርጋ ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ለማቋረጥ ስትሞክር የነበረችዋ የስደተኞች ጀልባ በመስጠሟ 6 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። እ.አ.አ. ከ2018 ጀምሮ ከ100,000 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በተመሳሳይ መልኩ በዚህ አደገኛ የስደተኞች መተላለፊያ መስመር ለማለፍ ሞክረዋል ተብሎ ይታሰባል።
 

14 August 2023, 15:04