ፈልግ

GERMANY-CULTURE-NATURE-EXHIBITION

ሳይንስ የከባቢ ብክለትን ወደሚቀንሰው ‘ዜሮ ልቀት ኢኮኖሚ’ የሚወስደውን መንገድ እየከፈተ ነው ተባለ።

የዓለም ሙቀት መጨመርን እና ብክለትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የፀሐይ ብርሃንን እንደ ብቸኛ የኃይል ምንጭ በመጠቀም የካርቦን ዳይኦክሳይድን (CO2) እና የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ወደ ታዳሽ ነዳጆች እና ሌሎች ጠቃሚ ኬሚካሎች መቀየር ችለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን ካርቦን ዳይኦክሳይድን እና ፕላስቲክን ወደ ታዳሽ ነዳጆች እና ሌሎች አስፈላጊ ምርቶች የሚቀይር በፀሐይ ብርሃን የሚሠራ ቴክኖሎጂ ፈጥረዋል።
ጥናታቸው በጆል ጆርናል ላይ የታተመላቸው ይህ የተመራማሪዎች ቡድን በተሳካ ሁኔታ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ዘላቂ ነዳጆች ጠቃሚ አካል ወደሆነው ሲንጋዝ እና ፕላስቲክን ደግሞ ወደ ግሊኮሊክ አሲድ የተባለ በፍራፍሬ ውስጥ የሚገኘውን እና በመድኃኒት ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥቅም ላይ ወደሚውለው ጠቃሚ ንጥረ ነገር መለወጥ ችለዋል።
ተመራማሪዎቹ ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ከባቢ አየር ላይ ያለውን ካርቦን ዳይኦክሳይድን እና የፕላስቲክ ቆሻሻን መጠን በመቀነስ የዓለም ሙቀት መጨመርን እና ብክለትን ለመቀነስ ይረዳል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ታዳሽ ነዳጆችን ማምረት የዛሬውን የኢነርጂ እጥረት ቀውስ ለመዋጋት እንደሚረዳ እና ዜሮ ልቀት ያለው ኢኮኖሚን ለማዳበር መንገዱን ሊከፍት ይችላል ተብሏል።

ካርቦን ዳይኦክሳይድን መቀየር

በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ለመቀነስ ፥ ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንደሚታወቀው በመደበኛነት ከአየር ላይ ይያዝና ከመሬት በታች ይከማቻል። ይህ ሂደት ግን የማይታወቅ የረጅም ጊዜ ተጽእኖዎች ይኖሩታል። በዚህ መሠረት ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ሌሎች ውህዶች ለመለወጥ የካርቦን ዳይኦክሳይድ የመቀየሪያ ዘዴዎች ተዘጋጅተዋል።
በተለምዶ ፥ አብዛኛው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልወጣ ቴክኒኮች የውሃ ኦክሳይድን እንደ ፀረ-ምላሽ ይጠቀማሉ ፥ ይህ ሂደት ደግሞ ከተለያዩ ምንጮች የሚመጡ የሃይል ግብአቶችን የሚጠይቅ አሰራር ነው።

በአሠራሩ ውስጥ አንዱ ብልሃት የፕላስቲክ አካልን መጠቀም ነው

የካምብሪጅ ተመራማሪዎች ግን ከውሃ ይልቅ ፕላስቲክን በመጠቀም የኃይል ፍላጎቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያቃልል የሚችል ዘዴ እንዳገኙ ያምናሉ።
የቫቲካን ዜና ከተመራማሪዎቹ ሁለቱ የሆኑትን ሳያን ካር እና ሞቲያር ራሃማንን አነጋግራ ስለ ሂደቱ እና ስለ ዓላማው የበለጠ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“የፕላስቲክ ኦክሳይድ ለሂደቱ በሙሉ የፀሐይ ኃይልን እንደ ብቸኛ የኃይል ምንጭ እንድንጠቀም ያስችለናል ፥ ይህም ከፕላስቲክ ይልቅ ውሃን ብንጠቀም ኖሮ የማይቻል ነገር ነበር” ሲሉ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሞቲያር ራማን ተናግረዋል ።
የዚህ አንድምታ ግልፅ ነው ፥ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን የካርበን ጉዳትን ሳናባባስ ወደ ታዳሽ ነዳጆች ሊቀየር ይችላል የሚለው ነው።

ወደ ዜሮ ልቀት ኢኮኖሚ

ዜሮ ልቀት ኢኮኖሚ ማለት ቁሶችን ወይም ምርቶችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል እና በማደስ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ስርዓት ሲሆን ፥ በተለይም ዘላቂነት ባለው ወይም ለአካባቢ ተስማሚ በሆነ መንገድ ምርትን ማስቀጠል ነው።
ቡድኑ ይህ ቴክኖሎጂ ወደፊት ጥቅም ላይ የሚውለው ዜሮ ልቀት ያለው ኢኮኖሚን ለማዳበር ሲሆን ይህም የቅሪተ አካል ነዳጆች አጠቃቀምን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግድ ተስፋ አድርጓል።
“ዓላማው ታዳሽ ነዳጆችን ከኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት የማምረት ሂደት ሲሆን ፥ ከዚያም ኢንደስትሪዎቹ ራሳቸው ያመረቱትን ነዳጅ የሚጠቀሙበት አሰራር ነው” ሲል የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ሳያን ካር አብራርተዋል።
“በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ነዳጅን ስንጠቀም ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ከባቢ አየር መልቀቃችን አይቀሬ ነው ፥ ግን ይህንን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ወደ ታዳሽ ነዳጅ መለወጥ ከቻልን ፣ የተጣራ ዜሮ ልቀት ኢኮኖሚ ስለመፍጠር ማሰብ እንችላለን” ብለዋል።
ይህ ደግሞ የፕላስቲክ ብክለትን በመቀነስ ጠቃሚ ምርቶችን ከፕላስቲክ ተረፈ ምርት ማምረትን ያካትታል።

የብሩህ ተስፋ ብልጭታ

“ቴክኖሎጂው ገና በጅምር ላይ ነው” ይላሉ የካምብሪጁ ራሃማን ፥  “በኢንዱስትሪ ደረጃ ሂደቱን ለመጠቀም የካርቦን ይዘትን ፣ የፀሐይ ኃይልን መሳብ ወይም የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልወጣ ዘዴዎችን ጨምሮ እያንዳንዱ ቁስ ወይም አካል መመቻቸት አለበት” ብለዋል።
ተመራማሪዎቹ ቴክኖሎጂውን በኢንዱስትሪ ደረጃ ለመጠቀም ቢያንስ አስር ዓመታት እንደሚፈጅ ገምተዋል።
“በአሁኑ ጊዜ የውጤቱን ብቃት እና ፍጥነት ለማሻሻል እየሰራን ነው ፥ ይህ ምንም ጥርጥር የለውም ጊዜ ይወስዳል ፥ ነገር ግን በራስ መተማመን እና በጣም ብሩህ ተስፋ አለን” በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል የካምብሪጅ ተመራማሪው ሳያን ካር።
 

12 July 2023, 15:09