ፈልግ

በጣሊያን የተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ያለው የአየር ሁኔታ በጣሊያን የተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ያለው የአየር ሁኔታ  (AFP or licensors)

ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን በዓለም ዙሪያ ተመዝግቧል ተባለ

በዚህ ሳምንት በደቡባዊ አውሮፓ እና በምስራቅ አውሮፓ ፣ በእስያ እንዲሁም በአብዛኛዎቹ የአሜሪካ ከተሞች ያልተለመደው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የመጨመሩ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በደቡባዊ አውሮፓ ሰፋፊ ግዛቶች በከፍተኛ የሙቀት መጠን መሸፈን በመቀጠላቸው የሙቀት መጠን መለኪያ ቁጥሮቹ በከፍተኛ ሁኔታ መጨር ማሳየታቸው ተነግሯል።
ሮም እስካሁን ከፍተኛውን የሙቀት መጠን የሆነውን 41.8 ዲግሪ ሴልሺየስ ያስመዘገበች ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ብቻ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በአንድ ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ አርጋ ሰብራለች። ዘላለማዊቷ ከተማ ተብላ በምትታወቀው ሮም ውስጥ ያሉ ቱሪስቶች ከውኃ ምንጮች ላይ ውሃ በፊታቸው ላይ በመርጨት እና ከአምፊ ቲያትር ቤቱ (ኮሎሲየም) ውጭ በተዘጋጁ ግዙፍ ማቀዝቀዣ ቬንትሌተሮች ስር በመቆም እራሳቸውን ለማቀዝቀዝ ሞክረዋል።
በከባዱ ሙቀት ምክንያት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ማክሰኞ ዕለት ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሲሆን ፥ በመላው ጣሊያን በሚገኙ ሆስፒታሎች ከሙቀት ጋር በተያያዘ ጉዳት ደርሶባቸው ለሚታመሙ ሰዎች ፈጣን ሕክምና ለማድረግ የሚያግዝ 'የሙቀት ጊዜ የህክምና ኮዶች' የተዘጋጀባቸው የድንገተኛ ክፍልን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር 20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የአውሮጳ ኅብረት የአደጋ ጊዜ ማስተባበሪያ ማእከል ለአብዛኛዉ የጣሊያን ግዛቶች ፣ ሰሜናዊ ምስራቅ ስፔን እና አብዛኛው የባልካን አገሮች የአየር ሙቀት መጠን በመጨመር ምክንያት ቀይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል።
ኃይለኛው የሙቀት ማዕበል በአህጉሪቱ በተለይም በግሪክ በርካታ የሰደድ እሳት እንዲነሳም ምክንያት ሆኗል ።
ነገር ግን በከባድ የሙቀት ማዕበል የተያዘው ደቡብ አውሮፓ ብቻ አይደለም። በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች እና በብዙ የቻይና አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት እየተሰቃዩ ሲሆን የምስራቅ እስያ ክፍሎች ደግሞ በከባድ ጎርፍ ተመተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአውሮጳ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑት ሃንስ ክሉጅ ገዳይ የሙቀት ማዕበሎችን እና ሌሎች አስከፊ የአየር ሁኔታዎችን እየተጋፈጥን ባለንበት እውነታ ፥ ዓለም ስለ ወደ ፊቱ ማሰብ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል። በማከልም በሰው ልጅ ላይ የህልውና ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ቀውስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመቅረፍ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
 

20 July 2023, 13:41