ፈልግ

የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ጀምሯል የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን መጠነ ሰፊ ዘመቻ ጀምሯል  (ANSA)

የእስራኤል ወታደሮች በዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የስደተኞች ካምፕን ኢላማ አድርገዋል ተባለ

እስራኤል በፍልስጤማዊያን በተያዘው ዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የስደተኞች ካምፕ በፍልስጤም ታጣቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምራለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ የፍልስጤም ግዛት ዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የስደተኞች ካምፕ ላይ በወታደሮች ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች በመታገዝ ቢያንስ አስር የአየር ላይ ድንገተኛ ጥቃቶችን ጀምራለች።
በሰው አልባ አውሮፕላኖች በተፈፀመ የአየር ጥቃት በትንሹ ሰባት ፍልስጤማውያን መሞታቸውን እና ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል።
እስከ ትናንቱ ሰኞ ድረስ ወደ 150 የሚጠጉ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች እና ወደ 1,000 የሚጠጉ ወታደሮች በካምፑ ላይ የሚደረገውን ከበባ አጠናክረው ቀጥለዋል ፥ ይህም የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት ማሳያ ብልጭታ ነው።
የእስራኤል ጦር ዘመቻው የጦር መሳሪያዎችን ለማውደም እና ለመውረስ ነው ብሏል።
የፍልስጤም የዜና ወኪል የሆነው ዋፋ እንደዘገበው የእስራኤል ወታደሮች ወደ ካምፑ የሚወስዱ መንገዶችን የዘጉ ሲሆን ፣ ብዙ ቤቶችን በመያዝ አልሞ ተኳሾችን በጣሪያ ላይ አስቀምጠዋል ብሏል።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ የሆኑት ነቢል አቡ ሩዲኔህ “የእኛ የፍልስጤም ህዝብ አይንበረከክም ፥ እጅ አይሰጥም ፥ ነጭ ባንዲራም አያውለበልብም ፤ በመሆኑም ይህን አሰቃቂ ጥቃት በመጋፈጥ በምድራቸው ላይ ጸንቶ ይኖራሉ” ብለዋል ።
በሌላ ቦታ ፥ በዌስት ባንክ ራማላህ አቅራቢያ አንዲት ፍልስጤማዊት የ21 ዓመት ወጣት በእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት መገደሏም ታውቋል።
 

04 July 2023, 14:17