ፈልግ

በየመን ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች በምእራብ ሆዴይዳ ግዛት በኮካ አውራጃ በሚገኝ ካምፕ የምግብ እርዳታ ሲቀበሉ። በየመን ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች በምእራብ ሆዴይዳ ግዛት በኮካ አውራጃ በሚገኝ ካምፕ የምግብ እርዳታ ሲቀበሉ።  (AFP or licensors)

ትኩረት የተነፈጉ ግጭቶች የሰውን ልጅ ከባድ ዋጋ ማስከፈላቸውን ቀጥለዋል ተባለ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተቀጣጠሉ ያሉትን ፥ እያንዳንዳቸው ከባድ የሰው ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ዋጋ የሚያስከፍሉ በርካታ ብጥብጦች እና ግጭቶችን በጎ ፈቃድ ያላቸው ወንዶች እና ሴቶች ጸሎት እንዲያደርጉ እና እንዳይዘነጉ ተማጽነዋል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 የተረሱ የሚመስሉ ግጭቶች በብዙ የዓለማችን ክፍሎች መባባሳቸውን ቀጥለዋል ፥ እያንዳንዳቸውም ከባድ የሰው ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ዋጋ ይስከፍላሉ። በአፍሪካ እንደታየው አለመረጋጋቱ ከየድንበሮቹ አልፎ ተስፋፍቷል።

ሱዳን

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ሱዳን ለሁለት ተቀናቃኝ ሃይሎች ታማኝ በሆኑ ወታደሮች መካከል በተቀሰቀሰ ዘግናኝ ግጭት ስትታመስ ቆይታለች። በዚያ ግጭት መጀመሪያ በካርቱም የበርካቶችን ደም በማፍሰስ ተጀመረ ፥ ከዚያም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኘው ዳርፉር ተዛመተ። ምንም እንኳን የአሃዙ ትክክለኛነት ባይረጋገጥም ግምቶች እንደሚያሳዩት ፥ ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን ከ1,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ሳህል እና ዲሞክርያሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ

አሁንም በአፍሪካ ፥ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ እስከ ቀይ ባህር ድረስ 5,400 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነው የሳህል ክልል ላይ እየተከሰተ ያለው ችግር በአሳሳቢነቱ ቀጥሏል። በዚሁ ክልል ለዓመታት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እና ጥበቃ የሚሹ ሆነዋል።
ከዚህም አልፎ በምስራቅ ኮንጎ ሰኔ 9 2015 ዓ.ም. በታጣቂ ቡድኖች የተፈፀመው አሰቃቂ ጥቃት የዓለሙን ማህበረሰብ ብዙ ነገር ያስታውሳል።

የመን ፣ ሶሪያ እና ዩክሬን

በሌላም ቦታ ፥ በየመን የተከሰተው ጦርነት ረጅም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁንም ድረስ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ስጋት ውስጥ ገብቷል። እንደሚታወቀው እ.አ.አ. በ2014 አማፂያኑ ዋና ከተማዋን ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛው የሀገሪቱን ክፍል በያዙ ጊዜ ሀገሪቱ ትንፋሽ በሚያሳጣ ሁከት ውስጥ ገብታ ነበር። ከዚህም አልፎ እ.አ.አ. በ2015 በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ወደ ጦርነቱ ሲገባ ሁኔታው ተባብሷል።
እ.አ.አ. ከ 2011 ጀምሮ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ያለቁባትን ሀገረ ሶሪያም ፥ የግጭቶቹ ዜናዎች በብዛት ባይገለጽም እንኳ እየደረሰ ያለው ግፍ ግን ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሩሲያ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ኢድሊብ ግዛት ላይ ባደረገችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቆ ፥ ድርጅቱ የጦርነቱ ሁኔታ በጣም እንዳሳሰበውም ገልጿል። ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ይህ ጥቃት በዚህ ዓመት ከተደረጉት ጥቃቶች እጅግ አስከፊው ሲሆን ፥ ተዋጊ ጄቶቹ በፍራ ፍሬ ገበያ አጠገብ የቦምብ ናዳ አውርደው ዘጠኝ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በዚህ ሁሉ ላይ በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ውጊያ በዓለም ላይ ላሉት ግጭቶች ሌላ ተጨማሪ ምስልን ይሰጣል።
 

03 July 2023, 13:01