ፈልግ

በአደገኛ መሻገሪያዎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ስደተኞች ከሚጠቀሙባቸው የጀልባ ዓይነቶች አንዱ በአደገኛ መሻገሪያዎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ስደተኞች ከሚጠቀሙባቸው የጀልባ ዓይነቶች አንዱ  (AFP or licensors)

የቆጵሮስ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች የ17 ዓመት የስደተኞች ጀልባ ካፒቴን በቁጥጥር ስር አዋሉ።

አሁን ላይ ባለው የአየር ንብረት ምክንያት የሜድተራኒያን ባህር ስለሚረጋጋ እጅግ በጣም ብዙ ሰው አደገኛውን የሜዲትራኒያን ባህር መሻገሪያዎችን አቋርጠው ለመሰደድ ያነሳሳቸዋል። በዚህም ምክንያት ሌላ የስደተኞች ቡድን በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ በምትገኘዋ የደሴት አገር እና ምስራቃዊ የሜድተራኒያን ባህር አከባቢ ላይ በምትገኘው ቆጵሮስ ደሴት ደርሷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተረጋጋውን የሜዲተራኒያን ባህር አጋጣሚ በመጠቀም ተጨማሪ የስደተኞች ቡድን ቆጵሮስ መድረሳቸው ታውቋል።
የአከባቢው ፖሊስ እንደገለጸው ባለፈው ሃምሌ 7, 2015 ዓ.ም. አርብ ዕለት 23 ስደተኞች የቆጵሮስ ደሴት ደቡብ ምስራቅ ክፍል በሆነችዋ ኬፕ ግሬኮ ላይ ተገኝተዋል።
በሚያስደንቅ ሁኔታ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 23 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችውን ጀልባ ስትመራ የነበረው በ17 ዓመት ታዳጊ እንደነበር ተነግሯል። ታዳጊውም ተይዞ በሚቀጥለው ሳምንት ፍርድ ቤት ይቀርባልም ተብሏል።
ልክ ከሁለት ቀናት በፊት ተመሳሳይ ጀልባ 23 ሰዎችን አሳፍራ በተመሳሳይ ቦታ ላይ ተገኝታ ወደ ሌላ የቆጵሮስ ወደብ እንደተወሰዱ ይታወቃል።
ሁሉም ተሳፋሪዎች ከሶሪያ እንደተሳፈሩ የታወቀ ሲሆን ፥ እያንዳንዱ ሰው በጀልባው ላይ ለመሳፈር በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን እንደሚከፍልም ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ሳምንት የቆጵሮስ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች 49 ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ከቆጵሮስ ደሴቶች ውስጥ አንዷ በሆነች እና በምዕራባዊ ጫፍ ላይ በምትግኘዋ በፓፎስ የባህር ዳርቻ ላይ በቁጥጥር ስር አውለዋል። የስደተኞቹም ጀልባ ባለፈው ሰኞ ዕለት ከሊባኖስ እንደተነሳች እና ወደ ጣሊያንም እያመራች እንደነበር ተነግሯል።
ቆጵሮስ በሜዲትራኒያን ባህር የሚደረገው የስደተኞች መተላለፊያ መንገድን አቋርጠው ከሚያልፉባት ከአውሮፓዊያን ህብረት ሃገራት የመጀመሪያዎቹ ረድፍ ላይ በመቀመጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ለመቀበል አበሳዋን እያየች ያለች ሃገር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
የቆጵሮስ ዋና ከተማ በሆነችዋ ኒኮሲያ ያለው መንግሥት እንደሚለው በማያቋርጥ ፍጥነት እየመጡ ያሉ ስደተኞች ምክንያት የጥገኝነት ጠያቂዎች ብዛት አሁን ካለው የደሴቲቱ ሕዝብ ውስጥ አምስት በመቶውን ይይዛሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ እስካሁን 72,778 ስደተኞች ከደቡብ ወደ አውሮፓ የገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 71,136ቱ በባህር ላይ በሚደረግ የጀልባ ጉዞ የደረሱ ስደተኞች እንደሆኑም ታውቋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስደተኞች የታጨቁ ፣ አሮጌ እና ለባህር ጉዞ የማይበቁ ጀልባዎች እንቅስቃሴ ችግር ለአካባቢው መንግስታት አሳሳቢ ሆኗል።
 

17 July 2023, 10:48