ፈልግ

የእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች በቴል አቪቭ የመኪና ጥቃት የደረሰበትን ቦታ እየመረመሩ የእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች በቴል አቪቭ የመኪና ጥቃት የደረሰበትን ቦታ እየመረመሩ  (ANSA)

የቴል አቪቩ ጥቃት እስራኤል በጄኒን የስደተኞች ካምፕ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት ተከትሎ ነው ተባለ

እስራኤል በጄኒን የስደተኞች ካምፕ በፍልስጤም ታጣቂዎች ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ወቅት ፥ በቴል አቪቭ በደረሰው የመኪና ጥቃት ሰባት ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ፥ ሦስቱ በከባድ ሁኔታ ቆስለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከቴል አቪቭ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ትናንት ሰኔ 27 2015 ዓ.ም. በደረሰው የመኪና ጥቃት ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን ሲሆን ፥ ከእነዚህም መሃል አንዲት ሴት ከባድ ጉዳት እንደደረሰባት ነው የሚያመላክቱት።
ጥቃቱ የተፈፀመው በሰሜናዊ ቴል አቪቭ የሃብታሞች መኖሪያ በሆነው ሰፈር ውስጥ ነው።
ጥቃቱን ያደረሰው እና በጥይት ተመትቶ የተገደለው ግለሰብ በዌስት ባንክ ውስጥ በኬብሮን አካባቢ የሚኖር የ23 ዓመት ወጣት መሆኑ ታውቋል።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን የሆነው ሃማስ ጥቃቱን በማድነቅ መግለጫ አውጥቷል። ቡድኑ ባወጣው መግለጫ በጄኒን ለተፈፀመው ‘የወረራ ወንጀል የመጀመሪያ ምላሽ’ ነው ብሏል።

ጄኒን ካምፕ ላይ የተደረገ ድንገተኛ ጥቃት

እስከ በቀደሙ ሰኞ ድረስ ወደ 150 የሚጠጉ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ወደ 1,000 የሚጠጉ ወታደሮች በጄኒን ካምፕ ላይ ከበባውን አጠናክረዋል ፥ ይህም አከባቢ የእስራኤል እና የፍልስጤም የግጭት ማዕከል ነው።
ጥቃቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእስራኤል ወታደሮች ቢያንስ 10 ሰዎችን ሲገድሉ ፥ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ በሁከቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወጥተዋል።
የእስራኤል ጦር እንደገለፀው ዘመቻው የጦር መሳሪያዎችን ለማውደም እና ለመውረስ ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተራድኦ ድርጅቶች እስራኤል በጄኒን በምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ መጠን የማስጠንቀቂያ ደውሉን አሰምተዋል።
 

05 July 2023, 16:07