ፈልግ

የእስራኤል እና  የፍልስጤም ግጭት የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት  (AFP or licensors)

በእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን መካከል ሠላም እና እርቅ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

እስራኤል በቅርቡ ወደ ዌስት ባንክ ገብታ ወታደራዊ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በቅድስት ሀገር ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በእሁዱ የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ሥነ ስርዓትን ተከትሎ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባደረጉት ንግግር በቅድስት ሀገር ውይይት ተደርጎ በእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን መካከል ሰላም እና እርቅ እንዲሰፍን ተማጽነዋል።
የሠላም ጥሪው የተደረገበት ምክንያት እስራኤል በቅርቡ በፍልስጤማዊያን ቁጥጥር ሥር ባለው ዌስት ባንክ ዉስጥ ወታደራዊ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ውጥረቱ በመባባሱ ምክንያት ነው ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት እስራኤል በሰሜናዊ ዌስት ባንክ አቅራቢያ በሚገኘው በጄኒን የስደተኞች ካምፕ ላይ ኢላማ አድርጋ የፈፀመችው ጥቃት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።
ብጥብጡ የጀመረው 150 የታጠቁ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና ወደ 1,000 የሚጠጉ የእስራኤል ወታደሮች በጄኒን ካምፕ ላይ ወታደራዊ ከበባን አጠናክረው ጥቃት በወሰዱበት ጊዜ ሲሆን ፥ ይህም ቦታ የእስራኤል እና የፍልስጤም የግጭት ማዕከል እንደሆነም ይታወቃል።
የእስራኤል ጦር ድርጊቱ የጦር መሳሪያዎችን ለማውደም እና ለመውረስ ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊነት ጽህፈት ቤት እንደገለጸው እስራኤል ባከናወነችው ወታደራዊው ዘመቻ ወቅት በጄኒን የአየር እና የምድር ጥቃት መጠነ ሰፊ እንደሆነ እና በተለይም የአየር ድብደባው ፍልስጤማዊያን በሰፈሩበት የስደተኞች ካምፕ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረበትም ተናግሯል።
ጥቃቱ እንደጀመረ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ካምፑን ለቀው ወጥተዋል።
በእስራኤል መግስት ለተፈፀመው ኦፕሬሽን ምላሽ እንደሆነ የተነገረው እና ማክሰኞ ዕለት በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ውስጥ በመኪና በተፈፀመ ጥቃት ሰባት ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን 3ቱ በከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
ፖሊስ እንዳረጋገጠው የዚህ የመኪና ጥቃት የተፈፀመው ፥ የ20 ዓመቱ ፍልስጤማዊ ወጣት በመኪናው ከገበያ አዳራሽ ውጭ ቆመው የነበሩትን እግረኞችን ሆን ብሎ በመግጨቱ ነው ተብሏል።
በዚህ ሳምንት መጨረሻ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ እና የሥራዎች ኤጀንሲ ባዘጋጀው ጉብኝት የውጪ ሃገራት ዲፕሎማቶች የልዑካን ቡድን የስደተኞች ካምፑን ጎብኝቷል።
ባብዛኛው የአውሮፓ ዲፕሎማቶች የሆኑበት 30 የልዑካን ቡድን በጥቃቱ የወደሙ ቤቶችን እና መሠረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።
 

10 July 2023, 15:05