ፈልግ

የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን የሚከበርበት ዋዜማ ላይ የአፍጋኒስታን አነስተኛ  የምግብ ነጋዴዎች ዳቦ በመንገድ ዳር እየሸጡ የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን የሚከበርበት ዋዜማ ላይ የአፍጋኒስታን አነስተኛ የምግብ ነጋዴዎች ዳቦ በመንገድ ዳር እየሸጡ  (ANSA)

በዓለም የምግብ ደህንነት ቀን፡- ‘የምግብ ወለድ በሽታዎችን ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላል’ ተባለ

የዓለም የምግብ ደህንነት ቀንን አስመልክቶ ሁለቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ፥ የህግ አውጭ አካላት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ብሄራዊ የምግብ ደህንነት ስርዓት እንዲመሰርቱ አሳሰቡ።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) በየዓመቱ ግንቦት 30 የሚከበረውን የዓለም የምግብ ደህንነት ቀንን በማስመልከት የዓለም የምግብ ደህንነት ስጋቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው ይወያዩበታል ተብሏል።
በዚህም ዓመት የሚከበረው ዓለም አቀፍ ቀን ላይ አጀንዳ አርገው በስፋት ለመወያየት ያቀዱት ይፋ በሆነው የምግብ ደህንነት አሰራሮችን እና ደረጃዎችን ወሳኝ ሚና ለማጉላት ያለመ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ማሪያ ኔሪያ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ከ200 የሚበልጡ ከቀላል እስከ ከባድ ያሉ በሽታዎች የተበከለ ምግብን በመውሰድ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ዶክተር ኔሪያ በሽታ ሲከሰት የምግብ ደህንነትን ግምት ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በምግብ ወለድ በሽታዎች ሙሉ በሙሉ መከላከል ስለሚቻልባቸው ዘዴዎች ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
“ስለ ምግብ ደህንነት የምናስበው ስንታመም ብቻ ነው ፥ ይህን ደጋግመን ልናስብበት ይገባል ፥ ምክንያቱም የምግብ ወለድ በሽታዎችን ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላልና” ሲሉም ተናግረዋል።
“ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ መመገብ የተመጣጠነ ምግብን እንድናገኝ እንድሁም የሰው ልጅ እድገት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ፥ ማንም ሰው ምግብ በመብላቱ መሞት የለበትም ፥ ምክንያቱም በዚህ ችግር የሚከሰቱ ሞቶችን አስቀድመን ልንቆጣጠር እንችላለን” ሲሉ ዶ/ር ኔሪያ አክለዋል።
ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ምግብ ጉዞ
የዓለም ጤና ድርጅት ረዳት ዋና ዳይሬክተሯ ህግ አውጪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች ከተቀመጡ ደረጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ጠንካራ ብሄራዊ የምግብ ደህንነት ስርዓቶችን መዘርጋት ያለውን ጠቀሜታ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። ዶ/ር ኔሪያ “የምግብ ደህንነት ደረጃዎች የሁሉንም ሰው ህይወት ይጠብቃሉ ፥ በተጓዳኝም ደህንነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ናቸው” ብለዋል። በተጨማሪም በምግብ ንግድ ላይ የተሳተፉ አካላት በሰራተኞቻቸው ፣ በአቅራቢዎቻቸው እና በባለድርሻ አካላት መካከል ‘የምግብ ደህንነት ባህልን’ እንዲያሳድጉ ይበረታታሉ። የትምህርት ተቋማት እና የስራ ቦታዎች ደግሞ ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አያያዝ አሰራሮችን በንቃት ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት አንዱ አካል የሆነው የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) በምግብ ሥራ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ የምግብ ንፅህና አጠባበቅ ደረጃዎችን እንዲያከብሩ ለመርዳት ያለመ ድረ-ገጽ አውጥቷል።
እንደ ‘ማጣቀሻ ገጽ’ የተገለፀው ድረ-ገጹ ስለግል ንፅህና መመሪያዎች ፥ ለምሳሌ የውጭ ጎብኝዎችን ወደ ምግብ ማምረቻ ቦታ ሲገቡ መውሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች የሚያስገነዝብ ፣ ተገቢ የእጅ አስተጣጠብ ሂደቶችን እና በወቅቱ የሚለበሱ ተስማሚ ልብሶችን በተመለከተ ምክሮችን ይሰጣል።
የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በዓመት 600 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታዎች እየተጠቁ እንደሆነ እና ለሁሉም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብን ማረጋገጥ የኤጀንሲው ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጿል።
 

08 June 2023, 13:30