ፈልግ

የዓለም መሪዎች በፓሪስ በተካሄደው አዲሱ የዓለም አቀፍ የፋይናንሺያል ስምምነት ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግሮችን እያዳመጡ የዓለም መሪዎች በፓሪስ በተካሄደው አዲሱ የዓለም አቀፍ የፋይናንሺያል ስምምነት ስብሰባ ላይ የመክፈቻ ንግግሮችን እያዳመጡ 

የተ. መንግስታት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሀገራትን ለመደገፍ አዲስ የፋይናንስ ስርዓት ሊዘረጉ ነው

በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈውን አዲስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነትን ለማዘጋጀት 40 የሚሆኑ የዓለም መሪዎች በፓሪስ ተሰብስበዋል። በፈረንሣይ ዋና ከተማ የተካሄደው ስብሰባ ለድህነት እና ለአደጋ የተጋለጡ ሀገራት ዕዳ ክፍያን የእፎይታ ጊዜ ስለመስጠትም አጀንዳው አርጎ ተወያይቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በፓሪስ የተሰበሰቡት መሪዎች እንደ አደገኛ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ቀውሶችን ለመቋቋም ለድሃ ሀገራት በመቶ ቢሊየን የሚቆጠር ዶላር መስጠት በሚቻልበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል።
በስብሰባው ላይ ከተካፈሉት ልዑካን መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ይገኙበታል። ‘የብሬተን ውድስ’ የሚባለው የጥቂት ሃገራት ስምምነት የዓለም ባንክን እና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ከፈጠረ ሰማንያ ዓመታት ገደማ በኋላ ድሃ አገሮችን ለመርዳት የሚውል አዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት እና ሥርዓት አቅርቧል። “መሰረታዊ የሆነ ማሻሻያ ከሌለ ለችግሩ ምንም አይነት ሁነኛ መፍትሄዎች አይኖሩም ፥ ለዚያም ነው ለአዲሱ ‘ብሬተን ዉድስ’ ስምምነት እና መንግስታት አንድ ላይ ተሰባስበው እንደገና እንዲመረምሩት ፥ እንዲሁም ለ 21 ኛው ክፍለዘመን የሚመጥን ዓለም አቀፍ የፋይናንሺያል ሥርዓት እንደገና እንዲዋቀሩ ጥሪ ያቀረብኩት” ሲሉ ጉተሬዝ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጉቴሬዝ አክለውም “የሚያስፈልጉትን ጥልቅ ተሀድሶዎችን የምናረገው እና ዛሬውኑ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ የምንችለው በማደግ ላይ ያሉ እና እየመጡ ላሉ አዳዲስ ኢኮኖሚዎች አፋጣኝ ፍላጎቶችን ለማሟላት ስንል ነው። ለዚህም ነው በየዓመቱ ለዘላቂ ልማት እና የአየር ንብረት ቀውስ የሚሆን አስፈላጊ ማበረታቻ 500 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኢንቨስትመንት እንዲደረግ ሀሳብ የማቀርበው” ብለዋል።
የአለም ባንክ ሃላፊው ለአበዳሪ ሃገራት የሚከፈለውን የዕዳ ክፍያ ለአፍታ መቋረጥን ጨምሮ በተፈጥሮ አደጋዎች ለተጠቁ ሀገራት የሚውል በርካታ የዕርዳታ እርምጃዎችን ከዚህን በፊት አውጀዋል ፥ ይህ የታዳጊ ሃገራትን ልኡካን ለሚመሩት ለባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ጆሮ የሚስማማ እንደ ጥኡም ሙዚቃ የሚሰማ ነበር።

ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል

በሞትሊ የሚመራው የታዳጊ ሀገራት ቡድን በአጀንዳው ላይ የሚያነሱትን ብዙዎቹን ርእሶች ‘ብሪጅታውን ኢኒሼቲቭ’ የሚል ስያሜን ሰጥተውታል።
የመጀመሪያዋ የባርቤዶስ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሜትሊ ፥ ድሃ ሀገራት የአየር ንብረቱ ለውጥ ላይ አስተዋጽኦዋቸው ትንሽ ቢሆንም ፥ በውጤቱ ግን በጣም እየተጎዱ ያሉት እነሱ ስለሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል። “አሁን ለእናንተ ንግግር እያደረኩ ባለሁበት ሠዓት ሃገሬን ጨምሮ ሌሎች በካሪቢያን እና በምስራቅ ካሪቢያን የሚገኙ ሃገራት በትሮፒካል ወይም ‘ብሬት’ በሚባለው አውሎ ንፋስ እየተጠቁ ናቸው” ሲሉ ለታዳሚዎቻቸው ተናግረዋል።
“ትናንት በጉባኤው ላይ ለመቆየት ወይም ለመሄድ መወሰን ነበረብኝ ፥ ሆኖም ግን ወደ ተግባራዊ እርምጃ መሄዳችን አስፈላጊ ስለሆነ መቆየትን መርጫለሁ” ብለዋል።
ሞትሊ አክለውም “ብሬት ከሚባለው ከትሮፒካሉ አውሎ ንፋስ በስተጀርባ ሌላ ዓይነት የአውሎ ንፋስ ስርዓት እንዳለ” ገልፀው ፥ “ይህ የክስተቱ አዲሱ እውነታ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
አስገዳጅ ውሳኔዎች የሚጠበቁ ባይሆኑም ፥ ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት ግን ጉባኤው ድሃ አገሮችን በገንዘብ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አጽንዖት ሰጥቶታል።
 

23 June 2023, 19:01