ፈልግ

 ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ስለ ዲጂታል ፕላትፎርሞች አጭር መግለጫ ለጋዜጠኞች ገለጻ ሲያደርጉ (2023.06.13) ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ስለ ዲጂታል ፕላትፎርሞች አጭር መግለጫ ለጋዜጠኞች ገለጻ ሲያደርጉ (2023.06.13) 

የተባበሩት መንግስታት ዋና ኃላፊ በአርተፊሻል ኢንተለጀንሲ ላይ ያሏቸዉን ስጋቶች ገለፁ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዲጂታል መድረኮች ላይ የመረጃ ታማኝነትን ለማስረፅ የተባበሩት መንግስታት አዲስ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት አባል ሀገራት በዲጂታል ስነ-ምህዳር ውስጥ ያለውን ‘ፈጣን የውሸት እና የጥላቻ ስርጭት’ መግታት አለባቸው ብለዋል ።

    አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሀገራት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) የሚያስከትለውን አደጋ በተለይም አመንጪዎቹ በጣም ጮክ ብለው የሚሰጧቸውን ማስጠንቀቅያዎች በቁም ነገር እንዲሰሙ ጠይቀዋል።
ጀነሬቲቭ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚባለው ዘርፍ ጽሑፍን ፣ ምስሎችን እና ሌሎች ሚዲያዎችን ማመንጨት የሚችል የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አይነት ነው።
ዋና ጸሃፊው ጉቴሬዝ ግን ስጋታቸውን ሲገልፁ ‘የዚህ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂው ፈጣን እድገት ሰዎችን ዲጂታል ቴክኖሎጂው በዓለም ላይ እያደረሰ ካለው ከባድ ጉዳት ማዘናጋት የለበትም’ ብለዋል።
“አሁን ባለንበት ዓለም በዲጂታል ዓለም ላይ ያለው የጥላቻ እና የውሸት መስፋፋት ከባድ ዓለም አቀፍ ጉዳት እያደረሰ ነው ፥ ግጭትን ፣ ሞትን እና ውድመትን እያቀጣጠለ ነው” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ጉቴሬዝ በዲጂታል መድረኮች ላይ የሚደረጉት የጥላቻ ንግግሮች እና የሀሰት መረጃዎች ዴሞክራሲን እና ሰብአዊ መብቶችን እንዲሁም የህዝብ ጤና እና የአየር ንብረት እርምጃዎችን እየጎዱ መሆናቸውን አስጠንቅቀዋል ።


የዲጂታል መድረኮችን አላግባብ መጠቀም


የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ማህበረሰቦችን በችግሮቻቸው ሲደግፉ እና የተገለሉ ወገኖችን ድምጽ ሲያሰሙ ፥ በሌላ መልኩ ይሄው ቴክኖሎጂ የፍርሀት ምንጭ ሲሆን እና ተስፋን የሚያጨልም መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ተናግረዋል። በማከልም “የዲጂታል መድረኮች ሳይንስን ለመገልበጥ እንዲሁም የተዛባ መረጃን እና ጥላቻን በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ለማሰራጨት አላግባብ ጥቅም ላይ ይውላሉ” ብለዋል።
ከዚያም ‘ግልጽ እና አሁናዊ ዓለም አቀፋዊ ስጋት’ ብለው በጠሩት ላይ ግልጽ እና የተቀናጀ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወስድ ተማጽነዋል።
የዚህ ዓለም አቀፋዊ ጥረት አካል የሆነው የተባበሩት መንግስታት የቅርብ ጊዜ ፖሊሲ በዲጂታል መድረኮች ላይ ስላለው የመረጃ ታማኝነት አጭር መግለጫ ነው። ይህ አጭር መመሪያ ለዓለም አቀፍ የተቀናጀ ምላሽ ማዕቀፍ ለማቅረብ እንደተዘጋጀ ተነግሯል።


ችግሩን መፍታት


የመረጃ ትክክለኛነት ማለት የመረጃ ሃቀኝነት ፣ ወጥነት እና አስተማማኝነት ማለት ነው። ይህ አሁን በሐሰት መረጃ ፣ በተዛባ መረጃ እና በጥላቻ ንግግሮች ምክንያት ስጋት ላይ ወድቋል ፥ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ እድገትን አደጋ ላይ ይጥላል ሲል የተባበሩት መንግስታት የፖሊሲ አጭር መግለጫው ገልጿል።
“ባህላዊ ሚዲያዎች ግጭት በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ለአብዛኞቹ ሰዎች ጠቃሚ የዜና ምንጭ ሆነው ቢቆዩም ፥ በዲጂታል መድረኮች ላይ የተንሰራፋው ጥላቻ ግን ብጥብጥ እንዲፈጠር እና እንዲባባስ አድርጓል” ሲል አጭር መግለጫው ተናግሯል።
የፖሊሲው ማጠቃለያ ሀሳቦች መንግስታት ሴራዎችን እና ውሸቶችን በሚያጋልጡ መመሪያዎች ዙሪያ አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ለመርዳት እና ሀሳብን የመግለፅ እና የመረጃ ነፃነትን ለመጠበቅ የታለመ የጥበቃ መንገዶችን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል ጉቴሬዝ ።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ዋና ኃላፊ እንዳሉት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሰጡ ምክሮች ዲጂታል ዓለምን የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሰብአዊ መብቶችን በመጠበቅ ረገድ የበለጠ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ይፈልጋሉ ።
በፖሊሲ ማጠቃለያው ውስጥ ከተካተቱት ሀሳቦች መካከል መንግስታት ፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሀሰት መረጃን ከማሰራጨት ለመታቀብ ዝግጁነታቸውን እንዲያሳዩ ፥ መንግስታት ለጋዜጠኞች ጠንካራ ጥበቃ ያለው ነፃ ፣ ገለልተኛ እና ለብዙሃን የሚዲያ ገጽታ ዋስትና ለመስጠት ቃል እንዲገቡ እና ሁሉን አቀፍ የሚዲያ ስነ ምህዳር እንዲኖር የዲጂታል ማዕቀፉ የሚወጡት ሁሉም የሚዲያ ውጤቶች ደህንነትን ፣ ግላዊነትን እና ግልጽነትን እና ሌሎችንም ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ለማረጋገጥ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ ያሳስባል።


ከሐሰተኛ መረጃ የሚገኝ ገቢ


“የተዛባ መረጃ እና ጥላቻ ከፍተኛ ተጋላጭነትን እና ትልቅ ትርፍን መፍጠር የለባቸውም” ሲሉ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናግረዋል።
ዋና ጸሃፊው ከጋዜጠኞች ‘የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና መንግስታት የዲጂታል ስነ-ምህዳሩን አስተማማኝ ለማድረግ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ እና ምን ያህል እንደሚተማመኑ’ ሲጠየቁ ፥ “ብዙ ትርፍ ከሚያስገኙ ንግዶች (የሚዲያ ካምፓኒዎችን ማለታቸው ነው) ጋር በመጋፈጣቸው ትልቅ ትግል ይፈልጋል” ብለዋል።
“ችግሩ ያለው አሁን ያለው የንግድ ሞዴል ከግላዊነት ፣ እውነት እና ከሰዎች ሰብአዊ መብቶች ይልቅ ተሳትፎን በማስቀደሙ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊ አብራርተዋል።
የፖሊሲ ማጠቃለያው ይህንን ጉዳይ በመጥቀስ “ለእነሱ ሐሰተኛ መረጃም ትልቅ ሥራ ነው” ሲል ገልፆ ፥ በአንዳንድ ክልሎች ፣ የፖለቲካ ሰዎች እና የግል ሴክተሮች የተቋቋሙ አንዳንድ የሕዝብ ግንኙነት ድርጅቶች ‘የሐሰት እና አሳሳች ይዘት ያላቸው መረጃዎች ቁልፍ ምንጮች’ ናቸው በማለት ያብራራል።
የፖሊሲ ማጠቃለያው በመስከረም ወር ከሚካሄደው የዘላቂ ልማት ግቦች ጉባኤ በፊት ውይይቶችን ለማሳወቅ የታቀዱ እና ከወጡት ተከታታይ 11 ሪፖርቶች በኋላ በቅርብ ጊዜ የወጣ ነው።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለ ሐሰትኛ መረጃ የተናገሩት


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቀደም ብለው የተሳሳተ መረጃን ችግር በጥብቅ ደብዳቤያቸው በሆነው ‘ፍራቴሊ ቱቲ’ ተናግረው ነበር ፥ የዲጂታል ዓለሙ ለህሊና እና ለዲሞክራሲያዊ ሂደት ስውር እና ወራሪ ዘዴዎችን የመጠቀም ችሎታ እንዳለው በመግለጽ የሐሰት ዜናዎችን እና የውሸት መረጃ ስርጭትን በማመቻቸት ይታወቃል ብለዋል።
ባለፈው ሰኔ 3 2015 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት በኖቤል ተሸላሚዎች የተረቀቀው እና የቀረበው የሰብአዊ ወንድማማችነት መግለጫ በተጨማሪም “የቴክኖሎጂን እና የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀሚያዎችን እናስቁም” የሚል እንድምታ ያለው መግለጫ አውጥቶ ነበር። “ከቴክኖሎጂው እድገት ይልቅ ወንድማማችነትን እናስቀድመው ፣ ያም ሲሆን በውስጡ ዘልቆ ይሰራጫል” ይላል መግለጫው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባ ባስተላለፉት መልእክት “ወንድሞች እና እህቶች በውሸት በሚናፈሰው የውዝግብ ባሕር ውስጥ የሚገኙ የእውነት መልህቆች ናቸው” ሲሉም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የተሳሳተ መረጃ ፣ ሀሰተኛ ዜና እና የጥላቻ ንግግሮች በዲጂታል ምህዳር ውስጥ እየተበራከቱ እና እየተሰራጩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመረጃ ታማኝነትን ማጠናከር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ተብሏል።
 

14 June 2023, 13:35