ፈልግ

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ  

ደቡብ አፍሪካ የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ጠየቀች።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአፍሪካ አህጉር የሚኖሩ ህዝቦችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እየጎዳ በመሆኑ ጦርነቱ ቶሎ እንዲቆም ጠይቀዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ስለ ሠላም አማራጮች ለመምከር ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ጋር በተገኙበት ወቅት ነው።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበበ

 የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጋር በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ከሚደረጉት ጥረቶች አንዱ የሆነው የአፍሪካ የሠላም ተልዕኮ አካል ሆነው በክሬምሊን ተገናኝተዋል።

ራማፎሳ ከሌሎች ስድስት የአፍሪካ መሪዎች ጋር ማለትም የኮሞሮስ ፣ የሴኔጋል እና የዛምቢያ ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ እና የኡጋንዳ ከፍተኛ ልዑካን ጋር በመሆን ሩሲያ ተገኝተዋል።
በአፍሪካ መሪዎች ደረጃ ከተደረጉት ይህ የመጀመሪያው የሆነው የዩክሬን ተልእኳቸው ፥ በቻይና ከተደረገው የሠላም ውጥን ሙከራ በኋላ የተደረገ መሆኑም ታውቋል።
የአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና የእርሻ እንደስትሪ በአብዛኛው ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚመጡት የምግብ እና የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ይህ የሠላም ተልዕኮ ለአፍሪካ ልዩ ጠቀሜታ አለውም ተብሏል።
ይሁን እንጂ ጦርነቱ በዓለም ላይ በጣም አስፈላጊ የሆኑት የዳቦ ግብአቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ እንቅፋት ሆኗል።
በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ንግግር ያደረጉት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ፥ ፑቲን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ የተከሰተውን ይህን የከፋ የመሳሪያ ጦርነት እንዲያቆሙ አሳስበዋል። “ይህ ጦርነት በድርድር እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እልባት ማግኘት አለበት” ብለዋል ራማፎሳ።
አክለውም ‘ሰባት የአፍሪካ መሪዎችን ያካተተው የልዑካን ቡድኑ የሚፈልገው ይህ ጦርነት እንዲያበቃ ግልጽ መልእክት ለማስተላለፍ ነው ፥ ይህን የምንልበት ምክንያት ደግሞ ይህ ጦርነት በአፍሪካ አህጉር እና በብዙዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ነው’ ብለዋል። ራማፎሳ ይሄን ያሉት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር መደበኛ ውይይት ከመደረጉ በፊት እንደሆነም ታውቋል።

አህጉራዊ መከራዎች

“እንደ አህጉር በኢኮኖሚያችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየደረሰብን ነው” ብለውም አሳስበዋል ፕረዜዳንት ራማፎሳ። የአፍሪካ መሪዎች የትጥቅ ግጭትን ተከትሎ የሠላም ድርድር እንዲካሄድም ሀሳብ አቅርበዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ለደቡብ አፍሪካ አቻቸው እንደተናገሩት ከዩክሬን ጋር በሚደረገው የሠላም ድርድር ላይ ተስፋ እንደማይቆርጡ ሲገልጹ “አፍሪካውያን ወዳጆቻችን በዩክሬን ቀውስ ላይ የያዙትን ሚዛናዊ አቋም እንቀበላለን” ብለዋል ፑቲን። አክለውም “ውድ ጓደኞች ፥ ግጭቱን ለመፍታት ያላችሁን ፍላጎት እናደንቃለን ፥ በዩክሬን ጉዳይ ላይ እንዲደረግ ለምትፈልጉት ሠላማዊ የሆነ የውይይት ሀሳብ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተናል” በማለትም ቃል ገብተዋል።
የአፍሪካ መሪዎች ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ መወገዝ አለባት ዬለባትም በሚለው ሃሳብ የተለያየ አቋም እንዳላቸውም ይታወቃል።
አሜሪካ በበኩሏ ‘በታህሳስ ወር ውስጥ ለሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን በድብቅ ሰጥታለች’ በማለት በደቡብ አፍሪካ ላይ ያላትን የገለልተኝነት ጥርጣሬዋን ገልጻለች። የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ግን ይህን ማስረጃ ያልቀረበበትን ክስ እያጣራሁ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ መሪዎቹ ሩሲያ ከመድረሳቸው በፊት ዩክሬንን ጎብኝተው ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮላዲሚር ዘሌንስኪ ጋር ተገናኝተው ተወያይተው እንደነበርም ተገልጿል።
ዘለንስኪ በበኩላቸው እ.አ.አ. በ2014 ሞስኮ ከግዛቷ የወሰደችውን የዩክሬን ክሬይሚያ ባሕረ ገብ መሬት ጨምሮ ሩሲያ የፖለቲካ እስረኞችን እንድትፈታ የአፍሪካ መሪዎች እንዲረዷቸው አሳስበዋል። በማከልም “እባካችሁ እ.አ.አ. ከ2014 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙትን የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቋቸው። እነዚህ እስረኞች በብዛት ክሬሚያውያን ሲሆኑ ሌሎች ብዙዎችም ይገኙበታል” ብለዋል።

ፍኖተ ካርታ

የዩክሬኑ መሪ ለአፍሪካ ልዑካን እንደተናገሩት “እባካችሁ ሩሲያ የፖለቲካ እስረኞችን እንድትፈታ ትጠይቃላችሁ? ይህ ከሆነ ለእኔ የፍኖተ ካርታችሁ ተልእኮ ወሳኙ ውጤት ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም ዜለንስኪ በኪዬቭ እና በሞስኮ መካከል የሠላም ድርድር የሚደረገው ሩሲያ ሁሉንም የዩክሬን ግዛት ለቃ ከወጣች ብቻ ነው ሲሉም አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እያለ ዩክሬን በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ ጦርነቶችን በማካሄድ የመልሶ ማጥቃት ጀምራለች።
ዜለንስኪ የሩስያን ‘ወረራ ሃይል’ ለመቀልበስ የሚዋጉትን “ጠንካራ እና ደፋር” ብለው የጠሯቸውን ወታደሮቻቸውን ለማመስገን በብዙ አገሮች የሚከበረውን የአባቶች ቀንን ተጠቅመዋል።
እነዚህ አባቶች ከየግንባሩ በሠላም ይመለሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ግልጽ አድርገዋል።
 

19 June 2023, 12:52