ፈልግ

የሩሲያ ወታደሮች የሩሲያ ወታደሮች 

የሩሲያው ፕረዚዳንት ወታደሮቻቸውን የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ስላደረጉት አስተዋጽኦ አመሰገኑ

በሩሲያ የመደበኛ ጦር አባል ያልሆነው ዋግነር ቡድን ከሩሲያ ጋር ያለውን ስምምነት በመጣስ በሩሲያ መከላከያ ላይ ያመጸው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነበር። የቡድኑ መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዢን በዩክሬን የሚገኘው የቡድናቸው ጦር ላይ የሩሲያ መከላከያ የቦንብ ድብደባ አድርጓል፣ በርካታ የቡድኑን አባላት ገድሏል በሚል ባቀረቡት ጥሪ ለሳቸው ታማኝ የሆኑ የቡድኑ አባላት ሮስቶቭ ኦንዶን የሚገኘውን የሩሲያ መከላከያ ጽሕፈት ቤት ተቆጣጥረው ነበር፡፡

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 በሞስኮ የሚገኘውን ወታደራዊ አመራር ከሥልጣን ለማስወገድ ጉዞ የጀመረው ቡድኑ ከሞስኮ ሳይደርስ በመሪው ፕሪጎዢን ትዕዛዝ ከጉዞው ታቅቧል። ሞስኮ የዋግነር ቅጥረኛ ቡድን ሤራ ነው ያለችውን የቅዳሜውን የከሸፈውን አመፅ ተከትሎ ከባድ ወታደራዊ ሃርድዌሩን ለማስረከብ ዝግጅት መደረጉን ተናግራለች። እርምጃው የተወሰደው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋግነርን ሊዘጉ እንደሚችሉ ካስታወቁ እና የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ወታደሮቻቸው ስላደረጉት አስተዋጽኦ ካመሰገኑ በኋላ ነው።
ከዋግነር ቅጥረኛ ቡድን ጋር በተደረገው ጦርነት ለሞቱት ወታደሮችም ወታደራዊ የሽኝት ሥነ ስርዓትም ተደርጎ ነበር።
የሰሞኑ የዋግነር የአመፅ እንቅስቃሴ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን ከመጡ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የተከሰተ ትልቁ ፈተና እንደነበርም ተነግሯል።
ፑቲን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከተቀሰቀሰው አመጽ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደፊት ወጥተው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት በመከላከላቸው ወታደሮቻቸውን አመስግነዋል።
የዋግነር ወታደራዊ ቡድን አባላት በትጥቅ የታገዘ አመፅ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ የሩሲያ ሕግ አስፈጻሚ አካላት ፣ ልዩ አገልግሎት ሰጪዎችና የሩሲያ ብሔራዊ ፀረ ሽብር ኮሚቴ ሊከሰት የሚችል የሽብር ጥቃትን ለመመከት በአንድ ላይ የቆሙበትም ነበር።የሩሲያ መሪ ወደ 2,500 ለሚጠጉ የጸጥታ ሃይሎች ፣ ብሄራዊ ጥበቃ እና ወታደራዊ ክፍል አባላት እና ህዝቡ የአመፃ ኃይሎችን በመቃወም ስላደረጉት አበርክቶ ሲናገሩ ፥ “የእኛ ውሳኔ እና ጀግንነት እንዲሁም የመላው ሩሲያ ማህበረሰብ መጠናከር ትልቅ ነበር እናም እነዚህን መሰናክሎች እና ግጭቶችን ለማስወገድ ወሳኝ ሚናም ተጫውቷል” ብለዋል።
የዋግነር ቡድን መሪ ፕሪጎዢን ፥ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉን እና በዩክሬን የሩሲያ ጦር መሪ ቫልሪ ግራሲሞቭ ብቃት የላቸውም ሲሉ ሲኮንኑ ከርመዋል። በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የቀረበውን የዋግነርን ቡድን በሚኒስቴሩ ቁጥጥር ሥር የማድረግ ሐሳብም ከዚህ ቀደም ተቃውመዋል። ባለፈው ዓርብ፣ ደግሞ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ያለውን የዋግነር ወታደሮች ማረፊያ በቦንብ መትቷል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ የሩሲያ መከላከያ ይህን ቢያስተባብልም ፥ የዋግነር ቡድን አባላት ከአዛዣቸው በደረሳቸው ትዕዛዝ መሠረት በደቡብ ሩሲያ የሚገኘውን ሮስቶቭ ኦንዶን የሚገኘውን የሩሲያ መከላከያ ተቆጣጥረው ሞስኮ የሚገኘውን መከላከያ ለመፈንቀል አልመው ጉዞ ጀምረው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 እንደተመሠረተ የሚታመነው የዋግነር ቡድን፣ በምዕራባውያኑ ዘንድ ሩሲያ የቀጠረችው የግል የውትድርና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ሰሞኑን ቡድኑ የፑቲንን መከላከያ ተቃውሞ ወደ ሞስኮ ሲያመራ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተሉ አስታውቀዋል፡፡ ቡድኑ ከ2015 ጀምሮ ከሶሪያ መንግሥት ጎን ተሠልፎ እንደሚዋጋና የነዳጅ ማውጫ አካባቢዎችን እንደሚጠብቅ ይናገሩም ነበር፡፡
በሊቢያ ወታደሮች እንዳሉት የሚታመነው ዋግነር፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የዳይመንድ በሱዳን ደግሞ የወርቅ ማዕድናት የሚገኙባቸውን ሥፍራዎች እንደሚጠብቅም ይታመናል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ የማሊ መንግሥት አይኤስን ለመዋጋት ቡድኑን የሚጠቅም ሲሆን ፥ የቡድኑ የገንዘብ ምንጭም በውጭ አገሮች የሚሰጠው የውትድርና አገልግሎት ነው፡፡
በተጨማሪም የሩስያ መንግስት ለዋግነር ቅጥረኛ ቡድን ሙሉ በሙሉ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል። ፑቲን እ.አ.አ ግንቦት 2022 እና ግንቦት 2023 መካከል ሩሲያ 86 ቢሊዮን ሩብል ወይንም አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ለቡድኑ አውጥታለች ብለዋል።

 ዋግነር ሊዘጋ ይችላል

ይሁን እንጂ ፑቲን የዋግነር ቡድን እንደሚዘጋ አስጠንቅቀው ፥ሩሲያውያን ለአገራቸው አንድነትና ላሳዩት ድጋፍ ምሥጋና የቸሩት ፑቲን ፥ የዋግነር ቡድን ወታደሮች ከሩሲያ መከላከያ ጋር ውል ገብተው አገልግሎታቸውን አንዲቀጥሉ አሊያም ወደ ቤላሩስ እንዲሄዱ አማራጭ አቅርበዋል። በቤላሩስ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አማካይነት በተደረገ ውይይትም አመፁ ሊቆም ችሏል ፡፡
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ለመከላከያ ሚኒስትራቸው እንደተናገሩት የዋግነር ወታደሮች ለቤላሩስ ጦርነትን በተመለከተ ‘በዋጋ የማይተመን’ መረጃ ሊሰጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል ።
ሆኖም ከክርምሊን ጋር በተደረገ ስምምነት የዋግነር መሪ ፕሪጎዢንና ለእሳቸው የታመኑ ወታደሮች ወደ ቤላሩስ ለማቅናት ሲስማሙ፣ ቀሪዎቹ በሩሲያ መከላከያ የሚቀላቀሉበት ካልሆነም ወደ አገራቸው የሚገቡበት ዕድል ተመቻችቷል። በቡድኑ አባላት ላይ ሊወሰድ የታሰበው ቅጣትም ተሽሯል። የቡድኑ መሪም ባለፈው ማክሰኞ በአውሮፕላን የቤላሩስ ዋና ከተማ ሚኒስክ ደርሰዋል።
ሆኖም በሩሲያ ጦር ኃይል ውስጥ ስላለው የዕዝ ሰንሰለት ጥያቄ አስነስቷል በመሆኑም በጎረቤት ዩክሬን የሚዋጉ የሩሲያ ወታደሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ወይም እንዲለቁ ሊያበረታታ ይችላል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ እንዳሉት የፑቲን አቋም በመዳከሙ የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት በሁሉም ግንባሮች መሻሻላቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አብዛኛው ወታደሮች የሆኑ ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ተብሎ ይታመናል ፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው ለመሰደድም ተገደዋል።
 

29 June 2023, 12:34