ፈልግ

ከኤል ሂሮ ደሴት ላይ ከአደጋ የታደጉ  ስደተኞች ከኤል ሂሮ ደሴት ላይ ከአደጋ የታደጉ ስደተኞች  (ANSA)

በካናሪ ደሴቶች ላይ ከጎማ ከተሰሩ ጀልባዎች ላይ ተሳፍረው የነበሩ ስደተኞችን ከአደጋ ማዳን ተችሏል።

በስፔን ካናሪ ደሴቶች ላይ በአነስተኛ ጀልባ ላይ ተሳፍረው ወደ አውሮፓ ሊሻገሩ ያቀዱ እና በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ቢያንስ 227 ስደተኞችን ከሞት ማትረፍ እንደተቻለ ነው የተነገረው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከጎማ በተሠሩ አነስተኛ ጀልባዎች ላይ ተሳፍረው በአደገኛ ሁኔታ ይጓዙ የነበሩትን ስደተኞች ማዳን መቻሉን ነው።
በሌላ ክስተት ባለፈው ረቡዕ ዕለት በግራን ካናሪያ ባህር ላይ ስደተኞችን ጭና የነበረችው ከጎማ የተሰራችው ጀልባ በመስመጥዋ ምክንያት ከ 30 በላይ ስደተኞች ሳይሞቱ አልቀረም ተብሎ ተሰግቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስደተኞች የታጨቁ አሮጌ እና ለባህር ጉዞ የማይበቁ ጀልባዎች እንቅስቃሴ ለአካባቢው መንግሥታት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
አደገኛው የአትላንቲክ የስደተኞች መተላለፊያ መንገድ በዓለማችን ከሚገኙ ገዳይ ስፍራዎች ከሆኑት እንደ አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው ዓመት ብቻ ቢያንስ 500 ስደተኞች ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ይላል።
በሌላ ቦታ ፥ በምስራቅ ሜዲትራኒያን ባህር ፥ በአያ ናፓ ሪዞርት አቅራቢያ ባለፈው ሰኔ 16 2015 ዓ.ም. ዕለተ አርብ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የነበሩትን ሁለት ጀልባዎች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ደርሰውላቸው 45 ሶርያውያን ስደተኞችን ከሁለቱ ጀልባዎች ማዳን ችለዋል።
ባለፈው ሳምንት በግሪክ የባህር ዳርቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳፍራ የነበረች የስደተኞች ጀልባ በመስጠሟ በትንሹ 78 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ እንደገለጸው 500 የሚደርሱ ሰዎች እስካሁን እንዳልተገኙ እና ከ750ዎቹ ተሳፋሪዎች አብዛኛዎቹ ከግብፅ ፣ ሶሪያ እና ፓኪስታን የመጡ መሆናቸውን አስታውቋል።
ልክ እንደ አትላንቲኩ የባህር መተላለፊያ መንገድ ፥ የሜዲትራኒያኑም መተላለፊያ በአውሮፓ ጥገኝነት ለሚፈልጉ ሰዎች አደገኛ መሻገሪያ መንገድ ተደርጎ ይቆጠራል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ እስካሁን 72,778 ስደተኞች ከደቡብ ወደ አውሮፓ የገቡ ሲሆን ፥ ከነዚህም መካከል 71,136 ስደተኞች በባህር ወደ ጣሊያን ፣ ግሪክ ፣ ስፔን ፣ ማልታ እና ቆጵሮስ መግባታቸውን አስታውቋል።
 

26 June 2023, 14:24