ፈልግ

የግሪክ 'አዲስ ዲሞክራሲ ፓርቲ' ፕሬዝዳንት ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ የግሪክ 'አዲስ ዲሞክራሲ ፓርቲ' ፕሬዝዳንት ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ  (ANSA)

የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር የሁለተኛ ዙር ምርጫን በጠባብ ውጤት አሸነፉ።

ይፋዊ ውጤት እንደሚያሳየው መራጮች በእሁዱ ምርጫ የግሪክ የለውጥ አራማጁን ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስን ለተጨማሪ አራት ዓመታት እንዲመሩ ዕድል ሰጥተዋቸዋል። ከከባድ የዕዳ ቀውስ እና ከሦስት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጎማዎች በኋላ የግሪክን ኢኮኖሚ ወደ መረጋጋት እና እድገት በማምጣት ተጠቃሽ ቢሆኑም አሁንም ከባድ ፈተናዎች እንደሚጠብቃቸውም አምነዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በግሪክ በመጀመሪያው ዙር የተደረገው ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስተር ኪሪያኮ ሚትሶታኪስ የሚመራው የመሀል ቀኙ የአዲሱ ዴሞክርሲ ፓርቲ፤ ከተቃውሚው የግራው ሲሪዛ ፓርቲ በከፍተኛ ልዩነት አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። ሆኖም ግን አሽናፊነቱ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል አብላጫ የፓርላም ወንበር ያስገኘ ባለመሆኑ ዳግም ምርጫን የሚያስቀር አልሆነም።
የግሪክ አጠቃላይ ህዝብ ብዛት ከአስራ አንድን ሚሊዮን የማይበልጥ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 9.8 ሚሊዮኑ ለመምረጥ ተመዝግቦ ነበር ተብሏል። በግሪክ የምርጫ ህግ መሰረት አሸናፊ ሆኖ መንግስት ለመመስረት፤ ከመራጩ ህዝብ 46 ከመቶ ድምጽ ማግኘትና ከ300 የፓርላማ መቀመጫም ቢያንስ 151 መቀመጫ ማግኘት ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ አንደኛ ወይም ሁለተኛ የሆነው ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመጣመር መንግስት ለመመስረት የሚችሉ ቢሆንም ይህ ግን በፓርቲዎቹ ባለው የአይዶሊጂና የፖሊሲ ልዩነቶች እንዲሁም የግሪክ ፓርቲዎች በጥምረት የመስራት ባህል ማነስ ምክኒያት ብዙ ግዜ አሰቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ከሶስቱ ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ፓርቲዎች በፓርላማ ለመግባት የሚያስፈልገውን 3 ከመቶና ከዚያ በላይ ድምጽ ያገኙ ቢሆንም ፤ አንዳቸውም ተጣምረው ለምስራት ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ነው ሲገልጹ ነው የቆዩት። በዚህ ምክኒያት ጠቅላይ ሚኒስተር ሚትሶታኪስ ያገኙትን ከፍተኛ ድጋፍና ውጤት መንግስት ለመመስረት ሳይሆን ዳግም ምርጫ ላማካሄድና ጠንክራ መንግስት ለመምስረት የሚያስችላቸውን አብላጭ የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት እንደሚጠቀሙበት በመግለጽ ለዳግም ምርጫ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ሁለተኛው ምርጫ ተካሂዶ የግሪክ ገዥው ወግ አጥባቂ የዲሞክራሲ ፓርቲ ድጋሚ ከተፎካካሪው ከሲሪዛ ፓርቲ በ23 ነጥብ በመብለጥ 40.5 ከመቶ ድምጽ አግኝቶ የማረጋገጫ ማህተሙን ማግኘቱ ታውቋል። በዚህም ምክኒያት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች
የመኪናዎቻቸውን ጡሩንባ በማሰማት ከተማ ዉስጥ በመዘዋወር ደስታቸውን አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቴንስ በሚገኘው የፓርቲው ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ደስታቸውን ለሚገልጹ ደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ ፥ “‘አዲስ ዴሞክራሲ’ ዛሬ በአውሮፓ ውስጥ ካሉት የመሀል ቀኝ ፓርቲዎች በጣም ኃይለኛው ፓርቲ ሆኗል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማከልም የፓርቲው ታማኝ መንግስታቸው ወደፊት የሚጠብቀውን ተግዳሮቶች እንዳይዘነጉ አሳስበዋል።
“ጓደኞቼ ተጠንቀቁ ይህ የፖለቲካ የበላይነት የትምክህት አሰራር ወይም ባዶ ቼክ አይደለም። ባለሥልጣኖቻችንን ሁሉ እንደገና የምጠይቀው ነገር ቢኖር ወደ መሬት ወርደው ህዝቡን እንዲያገለግሉ ነው” ብለዋል። “ዜጎች ብዙ ችግሮች አሉባቸው ፥ እነዚህንም ችግሮች እንድንፈታላቸው በካርዶቻቸው ጠይቀውናል ፥ ዛሬ የግሪክ ህዝቦች ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ ፥ በመሆኑም ድጋፍ ያልሰጡኝንም ዜጎቻችንንም ጭምር የማገልገል ግዴታ አለብኝ” ብለዋል።

ግሪኮች አሁንም እየታገሉ ነው

እ.አ.አ. በ2019 ወደ ስልጣን የመጡት ሚትሶታኪስና ፓርቲያቸው አገሪቱን ከገባችበት ችግር በማውጣት በኩል የተሻለ ስራ እንደሰሩና የግሪክን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጽታ እንዳሻሽሉት ነው የሚነገርላቸው። ግን አሁንም በግሪክ የኑሮ ውድነቱና በችግር ውስጥ ያለው ህዝብም ብዛት በአንጻራዊነት ከፍተኛ እንደሆነ ነው የሚነገረው ፤ ሆኖም ህዝቡ አሁንም ከፓርቲው ጋር መሆንን መርጠዋል።
በጠንካራ የፖለቲካ አቋም ባላቸው ቤተሰብ የሚደገፉት የ55 ዓመቱ የቀድሞ የባንክ ሰራተኛ ያሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሚትሶታኪስ ፥ ከወሳኙ የቱሪስት ኢንዱስትሪ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል። እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በተበደረች ሀገር ውስጥ የሥራ እድል ለመፍጠር እና ደሞዝ ለመጨመርም ቃል ገብተዋል።
የእሁዱ ምርጫ የተካሄደው በግሪክ የስደተኞች ጀልባ ላይ በደረሰ አደጋ ብዙ ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 500 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ በተነገረበት እና ከሶስት ቀናት ብሄራዊ ሃዘን በኋላ እንደሆነም ይታወቃል።
በዚህ ወር የደረሰው የስደተኞች ጀልባ አደጋ በግሪክ ውስጥ ስለ ስደተኞች ላይ የሚደረገውን ክርክርን አነቃቅቷል ፥ የግራ እና ቀኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ እራሳቸውን ስፓርታውያን ብለው የሚጠሩ ፀረ-ስደተኛ አቋም ያላቸውን ፓርቲዎችን ጨምሮ አብዛኛው የፓርላማ መቀመጫ አግኝተው ወደ ፓርላማ ገብተዋል።
 

27 June 2023, 16:15